Fana: At a Speed of Life!

የጤና ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት ችግር ፈቺ መሆን እንዳለበት ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ተቋማትን መገንባት ብቻ ሳይሆን የሚሰጡት አገልግሎት የህዝብን የጤና ችግር ፈቺ መሆን እንዳለበት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ ገልፀዋል።

የጤና ሚኒስቴር እና የክልል ጤና ተቋማት ተቆጣጣሪ አካላት የ2016 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የስራ አፈጻጻም ግምገማና ውይይት ከተለያዩ ክልል የተወጣጡ የክልል የጤና ተቆጣጣሪ አካላት በተገኙበት በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ ፍሬህይወት፤ በጤና ተቋማት ቁጥጥር እና ጥራት የማይነጣጠሉ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የጤና አገልግሎት ጥራት ከጎደለው በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ስለሚያስከትል ትኩረት ይፈልጋል ብለዋል።

የጤና ተቋማት ተደራሽነትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን ጥራቱን የጠበቀ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት የተጀመረው ጤናና ጤና ነክ የቁጥጥር ስራ ጥሩ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ተናግረዋል።

ተቆጣጣሪ አካላትም የጤና ተቋማት አገልግሎት ቁጥጥር፣ የባለሙያ ብቃት እና የመድሃኒት ቁጥጥር በማድረግ ላይ እንደሚገኙና በቀጣይነት ጥራት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ በበኩላቸው፤ የማህበረሰቡን ጥያቄ መሰረት በማድረግ በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በዚህም የጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የመድኃኒት ቁጥጥር እና የባለሙያ ብቃትን ከመጠበቅ አንፃር የተሻለ ስራ መሰራቱን አመልክተዋል።

የተጀመሩ ስራዎች ውጤት እያመጡ መሆኑንም በመጥቀስ፤ በዘርፉ የሚገጥሙ ማነቆዎችን በመቅረፍ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ይሰራል ብለዋል።

በደብሪቱ በዛብህ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.