የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መስተዳድር ም/ቤት ውሳኔዎችን አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 27ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
ምክር ቤቱ በቀረቡለት የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ላይ ተወያይቶ÷ ካላቸው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ፣ ከሚያስገኙት የሥራ ዕድል አኳያ 716 ሚሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 17 የግብርና እና 2 ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ወስኗል።
እስካአሁን የተወሰነላቸው የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች አፈጻጸምና ውጤታማነትም በቀጣይ ለመስተዳድር ምክር ቤቱ ሪፖርት እንዲቀርብ አቅጣጫ አስቀምጧል።
እንዲሁም በክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን የቀረበለትን የከተሞች ፈርጅ ለውጥ ጥናት ውጤት በተመለከተም ተወያይቶ፤ የቦንጋና ሚዛን አማን ከተሞች ወደ ፈርጅ አንድ፣ ታርጫ ከተማ ወደ ፈርጅ ሁለት እንዲሁም ዋካ፣ ቢፍቱ፣ ኢሳራባሌና ሸኮ ከተሞች ወደ ፈርጅ ሶስት እንዲያድጉ ወስኗል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ በስድስት ረቂቅ ደንቦች ላይ ተወያይቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ ውሳኔ ማሳለፉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
ደንቦቹም÷ የገጠር መሬት መጠቀሚያ ክፍያና የግብርና ሥራ ገቢ ግብር፣ የህግ ታራሚዎችና የቀጠሮ እስረኞች አያያዝ፣ የክልሉ የማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የገበያ ድጋፍ፣ የፋይናንስ አስተዳደር እንዲሁም የምግብ ስርዓት እና ስርዓተ ምግብ ምክር ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንቦች መሆናቸው ተገልጿል፡፡