Fana: At a Speed of Life!

ህብረተሰቡን የልማት ባለቤት በማድረግ የሚነሱ ጥያቄዎችን መመለስ ይቻላል – አቶ ጥላሁን ከበደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ህብረተሰቡን በማሳተፍ የልማት ባለቤት በማድረግ የሚነሱ ጥያቄዎችን መመለስ እንደሚቻል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡

የክልሉ ምክር ቤት እያካሄደ ባለው መደበኛ ጉባዔ ላይ የክልሉን የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ላቀረቡት ርዕሰ መስተዳደሩ÷ የምክር ቤት አባላት ጥያቄ እና ማብራሪያ አቅርበዋል።

የግብርና ግብዓት ወቅቱን ጠብቆ እንዲደርስ፣ የጤና፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ የውሃ ተቋማትን ግንባታን በሚመለከት ጥያቄ አንስተዋል፡፡

ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት አቶ ጥላሁን ከበደ÷ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በክልሉ ያለውን አቅምና ፀጋ በቅድሚያ ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡን በማሳተፍ የልማት ባለቤት በማድረግ የሚነሱ ጥያቄዎችን መመለስ ይቻላል ነው ያሉት፡፡

የውስጥ ገቢ አቅምን በማሳደግ ግብር በተገቢው መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

የግብርና ቴክኖሎጂ ከመጠቀም አኳያ ክልሉ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው÷ ከችግሩ ለመውጣት ርብርብ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡

የኦሞ ወንዝ ከመሙላት ጋር ተያይዞ 70 ሺህ ያህል የተፈናቀሉ ዜጎችን የመደገፍና በቋሚነት መኖሪያ የማመቻቸት ስራ እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል፡፡

የመብራት ኃይል ተደራሽነትን በሚመለከት የገጠር ወረዳ ማዕከሎችን በቅድሚያ ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

የተዘረጋውን የመብራት ኃይል መስመሮችን ከስርቆት የመከላከል ስራ ትኩረት የሚያስፈልገዉ ጉዳይ መሆኑንም አሳስበዋል፡፡

የተጀመሩ የመንገድ ስራዎችን ለመጨረስና አዳዲስ ለመጀመር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

ክልሉን የሰላም ተምሳሌት ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸው፤ ባህላዊ የግጭት አፈታትን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምና አንድነት እንዲረጋገጥ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት የተሰሩ ስራዎችን በሚመለከት ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ÷ የቀረበው ሪፖሪት በምክር ቤት አባላት በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።

በማቴዎስ ፈለቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.