Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የ7 ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 6 ሺህ 92 የላብራቶሪ ምርመራ 86 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ሲገኝባቸው የ7 ሰው ህይወት ማለፉን የጤና ሚኒስት ዶ/ር ሊያ አስታወቁ።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 2 ሺህ 20 መድረሱን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዛሬው እለት ባወጡት ሪፖርት አመላክተዋል።

ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ ሁሉም ሰዎች ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ እድሜያቸው ከ7 እስከ 87 ዓመት የሆኑ 51 ወንዶችና 35 ሴቶች ናቸው።

ቫይረሱ በምርመራ ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ 66 ሰዎች ከአዲስ አበባ ሲሆኑ፥ 1 ሰው ከአማራ ክልል፣ 7 ሰዎች ከትግራይ ክልል፣ 7 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ ከደቡብ ክልል 4 ሰዎች እንዲሁም ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 1 ሰው ናቸው።

ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተገናኘ 2 ወንድ እና 4 ሴቶች የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንዲሁም 1 ሰው ከኦሮሚያ ክልል ህይወት ማለፉን ገልፀዋል።

ህይወታቸው ካለፉ ግለሰቦች ውስጥም በአዲስ አበባ ከዚህ ቀደም በኤካ ኮተቤ ሆስቲታል ውስጥ በህክም ላይ እያለች በሰላም እንደተገላገለች የተገለፀችውን እናት ጨምሮ 4ሰዎች (3ሰዎች ከአዲስ አበባ 1 ሰው ከኦሮሚያ ክልል)በአስክሬን ምርመራ በተደረገ ምርመራ የኮሮና ቫይረስ እንደነበረባቸው የታወቀ ናቸው፡፡

እንዲሁም 3ሰዎች ህክምና ሲደረግላቸው ቆይተው ሕይወታቸው አልፏል፡፡

በአጠቃላይ በቫይረሱ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 27 ደርሷል።

የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በህልፈተ ህይወታቸው የተሰማቸውን ሀዘን እየገለጹ፤ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል።

በሌላ መልኩ በትላንትናው ዕለት 63 ሰዎች ያገገሙ ሲሆን፥ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 344 መድረሱንም አስታውቀዋል።

በፀና የታመሙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 32 ደርሷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.