Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የመንግስት ሠራተኞች ድልድል ትግበራ በዛሬው ዕለት ይጀምራል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስት ሠራተኞች ድልድል ትግበራ በዛሬው ዕለት እንደሚጀመር የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ ጣሰው ገብሬ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ ÷በ16 ተቋማት የሠራተኞች ምዘና እና ምደባ ለማካሄድ የዝግጅት ምዕራፉ ተጠናቆ ወደ ተግባር ለመግባት የሰራተኞች ድልድል መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የአሰራር ስርዓት ለውጥ ማስፈለጉ፣ የተጠያቂነት ስርዓት አለመኖር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር፣ የብቃት ችግሮች መኖራቸውና የሥራና ሰራተኛ አለመመጣጠን ለለውጡ ምክንያት መሆኑን አንስተዋል።

ለዚህም በዝግጅቱ የተለያዩ ጥናቶች፣ አዋጅ 84/2016 መፅደቁን፣ የአደረጃጀትና ሌሎች ሥራዎች መከናወናቸውን፣ የደንብና መመሪያ ዝግጅት መካሄዱን እና ወደ ሥራ የገቡ መመሪያዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ከ16 ተቋማት ጋርም የቴክኖሎጂ ልየታና ዝግጅት ሥራዎች መሰራታቸውን ነው የጠቆሙት።

በዚህም 42 አዳዲስ የአይሲቲ መሰረተ- ልማቶች ወደ ሥራ እንደሚደቡ ገልጸው ፥ በሦስተኛ ወገን የሚሰሩ አገልግሎቶችና ተቋማት መለየታቸውን አስረድተዋል፡፡

በሠራተኞች ብቃት ምዘና ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ መርሆዎች መተግበራቸውን ጠቅሰው÷የተሰጠውን ፈተና ያለፉት 99 ነጥብ 9 በመቶ ያህሉ እንደተመደቡ አረጋግጠዋል፡፡

ፈተናውን ያላለፉ ደግሞ ከደረጃ ዝቅ ማለት እንዲሁም ሠራተኞችን ለማመጣጠን ወደ ክፍለ ከተማና ወረዳ ምደባዎች መካሄዳቸውን አስገንዝበዋል፡፡

ምድባው ወደ ተግባር የሚገባው ከዛሬ ጀምሮ ሲሆን ፥ ከ17 ሺህ በላይ ሠራተኞች ስልጠና መውሰዳቸውም ተመላክቷል።

በአፈወርቅ እያዩ እና መራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.