የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከዓለም ባንክ የማማከር ሥራ ፈቃድ አገኘ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በዓለም ባንክ ፋይናንስ በሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ላይ የኢንጂነሪንግ የማማከር ሥራዎችን በራሱ አቅም እንዲሠራ ከባንኩ ፈቃድ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
ከባንኩ ጋር በተደረጉ ውይይቶች ተቋሙ የማማከር ሥራውን በራሱ አቅም እንዲያከናውን ከስምምነት መደረሱን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢንጅነሪንግ ዘርፍ የማስተላለፊያ መስመሮች ሲስተም ዲዛይን መምሪያ ዳይሬክተር ያሬድ ፍቃዱ ተናግረዋል፡፡
በዚሁ መሠረትም÷ ተቋሙ የሰርቬይንግ፣ የቅድመ ዲዛይን፣ የቴክኒካል ስፔሲፊኬሽን ዝግጅት፣ የፍላጎት መግለጫ፣ የኮንትራት አሥተዳደር እና የኮንስትራክሽን ቁጥጥር ሥራዎችን በራስ አቅም እንዲሠራ ፈቃድ አግኝቷል ብለዋል፡፡
በዓለም ባንክ ፋይናንስ በሚሠሩ ፕሮጀክቶች እንደ ወራቤ – ቡታጅራ የማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ፕሮጀክት፣ ፕሮቴክሽን ሪፍሬሽመንት ፕሮጀክት እና በራስ ፋይናንስ እየተሠሩ ያሉ ፕሮጀክቶች አፈፃፀማቸው ተገምግሞ በራስ የማማከር ዕድሉ መገኘቱን አብራርተዋል፡፡
ሙሉ የማማከር ሥራ መገኘቱም ተቋሙ የነደፈውን የሦስት ዓመት የስትራቴጂ ዕቅድ ለማሳካት እና የውጭ ምንዛሬን ለማዳን አስተዋጽኦው የጎላ ነው ማለታቸውን ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡