Fana: At a Speed of Life!

የተፈጥሮ ሀብቶችን ለኢኮኖሚ ጥቅም ለማዋል የተጀመሩ ሥራዎች እንደሚቀጥሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለኢኮኖሚ ጥቅም ለማዋል በመንግሥት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

በሚኒስትሯ የተመራ የፌዴራል ልዑክ በክልሉ የድጋፍና ክትትል ሥራ እያከናወነ ነው።

በቤንች ሸኮ ዞን የልማት ሥራዎችን በጎበኙበት ወቅት ሚኒስትሯ እንዳሉት÷ ለግብርና ሥራ ምቹ ከሆነው የመሬት፣ የውሃና የደን ሀብት በተጨማሪ በክልሉ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ አልምቶ መጠቀም ይገባል፡፡

አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ሀብቱን አልምቶ ለመጠቀም እያደረገ ያለው ጥረት ውጤታማ ሆኖ ኢኮኖሚውን መደገፍ እንዲችል በአካባቢው መሠረተ ልማትን ማሟላት እንደሚገባም ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

በዋናነት አርሶ አደሮቹ ምርታቸውን ወደ ገበያ ለማውጣት እየገጠማቸው ያለውን የመንገድ መሠረተ ልማት ችግር ለመፍታት በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት መስጫዎች ለገጠሩ የህብረተሰብ ክፍል እንዲደርሱ በቀጣይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ በሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የተመራ የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ በሐረሪ ክልል ባካሄደው የክትትልና ድጋፍ ሥራዎች ላይ ከክልሉ የካቢኔ አባላት ጋር መክሯል፡፡

ሚኒስትሯ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በየዘርፉ የተከናወኑት ተሞክሮ የሚሆኑ አበረታች ሥራዎች ሊጠናከሩ ይገባል።

በተለይም በጤና፣ ቱሪዝም፣ በከተማ ልማትና በሌሎችም ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች በተሞክሮነት የሚወሰዱ ናቸው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.