የተለያዩ ሚኒስትሮች በክልሎች ሲያካሂዱት ለቆዩት ጉብኝት ግብረ መልስ ሰጡ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል የድጋፍና ክትትል ቡድኖች በተለያዩ ክልሎች በተከታታይ ቀናት ሲያካሂዱ የቆዩትን ጉብኝት አጠናቅቀዋል፡፡
የፌዴራል የድጋፍና ክትትል ቡድን ባለፉት 10 ቀናት በአማራ ክልል ሦስት ማዕከላት ያካሄደውን ድጋፋዊ ጉብኝት አስመልክቶ በባህርዳር ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡
የልዑኩ አስተባባሪ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በውይይቱ ላይ እንዳሉት ፥ መንግስት ብልፅግናን ለማረጋገጥ የ10 ዓመት ስትራቴጅክ ግብ ይዞ እየሰራ ይገኛል።
በአማራ ክልል ከዚሁ ስትራቴጂክ ግብ የተቀዱ ውጤታማ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን መታዘባቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቅሰው፥ የክልሉ አመራርም ሰላምን ብሎም ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ ባደረገው ርብርብ ውጤት እየተገኘ መሆኑን አመልክተዋል።
በቀጣይ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂነት በማሸጋገር የላቀ የልማት አፈፃፀም ለማስመዝገብ ክልሉ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የድጋፍ ቡድኑ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ብለዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው ፥ የፌደራል የድጋፍና ክትትል ቡድን በቆይታው ያካሄደው ድጋፋዊ ጉብኝት የመፈፀም አቅምን ለማሳደግ ትልቅ እገዛ አለው ሲሉ ገልጸዋል።
ቡድኑ የሚያቀርበውን ግብረ መልስ እንደ ግብዓት በመጠቀምም በቀጣይ ለዘላቂ ሰላም መስፈንና ልማትን በማረጋገጥ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚጠቀሙበት አስረድተዋል።
በተመሳሳይ በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የተመራው ልዑክ ባለፉት አስር ተከታታይ ቀናት በሲዳማ ክልል ባካሄደው ምልከታና በተሰሩ አጠቃላይ ሥራዎች ላይ ግብረ መልስ ሰጥቷል።
አቶ አሕመድ ሽዴ ፥ ልዑኩ በክልሉ ቆይታው በገጠር እና በከተማ አጠቃላይ የተሰሩ ሥራዎችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል ብለዋል፡፡
በምልከታውም ጥሩ አፈፃፀም ላይ ያሉ ሥራዎች እንዳሉ ሁሉ መሻሻል ያለባቸው ሥራዎች መኖራቸውን ለክልሉ ካቢኔ አባላት አማብራራታቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ÷ መስተካከል ያለባቸውን በክልሉ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን በቀጣይ ወራት ውስጥ ከካቢኔያቸው ጋር እንደሚያስተካክሉ ገልጸው÷ ከክልሉ አቅም በላይ በሆኑ ሥራዎች ላይ የፌዴራሉ መንግስት እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም የፌዴራል ከፍተኛ የሱፐርቪዥን ቡድን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሲያካሂድ የቆየውን ድጋፋዊ የመስክ ምልከታ አጠናቅቆ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት የመስክ ምልከታ ግብረ-መልስ በአርባ ምንጭ ከተማ ሰጥቷል፡፡
የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም የተመራው ልዑክ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ፣ ኮንሶ እና አሪ ዞኖች የተለያዩ ወረዳና ቀበሌ ተዘዋውሮ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ዙሪያ ለአንድ ሣምንት የቆየ የመስክ ምልከታ ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወቃል።
ተጨማሪ መረጃ ጀማል ከዲሮ እና ተመስገን ቡልቡሎ