በአፋር ክልል ያለውን ሀብት አልምቶ በመጠቀም ረገድ የተጀመሩ ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል የሚገኘውን ሀብት አልምቶ በመጠቀም ረገድ የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።
በአቶ መላኩ አለበል የተመራ የፌዴራል ልዑክ በአፋር ክልል ሲያደርግ የቆየው ድጋፋዊ ጉብኝት ተጠናቅቋል።
በማጠቃለያ ውይይቱ ላይም ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር÷ በክልሉ ያለውን ሀብት አልምቶ ለጥቅም ማዋሉ ላይ የተጀመሩ አበረታች ሥራዎች መኖራቸውን በመጥቀስ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
በክልሉ ዜጎች በማኅበር ተደራጅተው በተሰማሩባቸው የልማት ሥራዎችም ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል፡፡
የአፋር ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አወል አርባ በበኩላቸው÷ የድጋፍ ልዑኩ በጥንካሬና በውስንነት የሰጠው ሐሳብ ላይ በትኩረት እንደሚሠሩ ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተመሳሳይ በፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ያደረገውን ምልከታ በማጠናቀቅ ከክልሉና ዞን አመራሮች ጋር ተወያይቶ ግብረ መልስ ሰጥቷል፡፡
በዚህም በሠላምና ፀጥታ ዘርፍ፣ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በግብርና፣ በአዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ፣ በሌማት ትሩፋት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አበረታች በመሆናቸው ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል፡፡
ክልሉ ባለው አቅም ልክ ገቢ ማመንጨት እንዲችልም የፖሊሲ እና የሕግ ማዕቀፍ ማበጀት እንደሚስፈልግ ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል በፌደራል መንግሥት የተጀመሩ መሠረተ ልማቶች ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ ልዑኩ ከሚመለከታቸው የፌዴራል መንግስት አካላት ጋር እንደሚነጋገር አስታውቀዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በበኩላቸው የልዑኩ ጉብኝትና ግብረ መልስ ለክልሉ አቅም መሆኑን ጠቅሰው÷ መልካም አፈጻጸሞችን በማጠናከር ክፍተቶችን ለመሙላት እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም በሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል የተመራ ልዑክ በድሬዳዋ ከተማ ለአራት ቀናት ያደረገውን ምልከታ በማጠናቀቅ የአሥተዳደሩ አመራሮች በተገኙበት የማጠቃለያ ግብረ መልስ ሰጥቷል፡፡
በዚህም ልዑኩ የመስክ ምልከታውን መነሻ በማድረግ ተጠናክረው መቀጣል ያለባቸውን ጉዳዮች በመጠቆም ለቀጣይ ሥራዎችም የትኩረት አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡