Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ጥቅሟ እንዲከበር የጋራ ጥረትና ትብብር ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ጥቅሟ በተገቢው መልኩ እንዲከበር የጋራ ጥረትና ትብብር ወሳኝ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣይ በብሪክስ ማዕቀፍ ለሚኖራት ተሳትፎ የቅድመ ዝግጅት ምክክር በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ተካሂዷል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃፋር በድሩ÷ብሪክስን የመቀላቀል አንዱ ዓላማ በሁሉም ምቹ ሁኔታዎች ውስጥ ትብብርን መመስረት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ይህም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅና የህዝቡን የልማት ፍላጎቶች ለመመለስ አጋርነትን ማስፋፋት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ጥቅሟ በተገቢው መልኩ እንዲከበርም የጋራ ጥረትና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

በመድረኩ የብሪክስ ማዕቀፍና የኢትዮጵያ ተሳትፎ ሂደት እንዲሁም ተቋማቶቿ የሚኖራቸውን ሚና በሚመለከት ሁለት የመነሻ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በምክክር መድረኩ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከአሰላሳይ ቡድንና ከሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት የተወጣጡ ተወካዮች መሳተፋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በቀጣይ ሚያዚያ ወር ከብሪክስ የባለሙያዎች ም/ቤትና ከብሪክስ ሲቪል ፎረም የተወጣጣ ልዑክ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.