Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቱ የሁለት ግለሰቦችን ሰነድ ሳያረጋግጡ ወደ ኡጋንዳ እንዲሄዱ አድርገዋል የተባሉ ሰራተኞችን ጉዳይ ተመለከተ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ሁለት ግለሰቦች የያዙትን ሀሰተኛ የቢጫ ወባ ክትባት ካርድ፣ ፖስፖርትና ቪዛ በተገቢው ሳያረጋግጡ እና ዳታ ላይ እንደመዘገቡ አስመስለው ወደ ኡጋንዳ እንዲሄዱ አድርገዋል ተብለው በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የኢሚግሬሽንና የአየር መንገድ አራት ሰራተኞችን ጨምሮ የስድስት ግለሰቦችን የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ተመለከተ።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ ናቸው የተባሉት ኤፍሬም ታዬ፣ አስፋው ቢፍቱ፣ ተክለወይን ተስፋይ፣ ኒያት ፀጋይ ሲሆኑ ወደ ኡጋንዳ ተጉዘው ሀሰተኛ ፓስፖርት፣ ሀሰተኛ የቢጫ ወባ ክትባት ካርድ በመያዛቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎች ደግሞ ኡጁሉ ኡጁሉ ኡዋርና ኒያል ባንግ ቤል ናቸው።

እነዚህ ተጠርጣሪዎችን ከኢሚግሬሽንና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጎ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ተገልጿል።

መርማሪ ፖሊስ በ1ኛ እና 2ኛ ተጠርጣሪዎች ሁለቱ ግለሰቦች የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም ወደ ኡጋንዳ ለመሄድ ከምሽቱ 4:45 በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በቀረቡበት ወቅት የመንገደኞች ጉዞ ዳታ ላይ ሳይመዘግቡ እንደተመዘገቡ አስመስለው ግለሰቦቹ እንዲያልፉ ማድረጋቸውን የጠቀሰው መርማሪ፤ 3ኛ እና 4ኛ ተጠርጣሪዎች ደግሞ የጉዞ ሰነዳቸው ሀሰተኛ ሆኖ ሳለ ሳያረጋግጡ ወደ ኡጋንዳ እንዲሄዱ ማድረጋቸውን ጠቅሶ የስራ ኃላፊነታቸውን ያለአግባብ መገልገል ሙስና ወንጀል በመጠርጠራቸው የምርመራ ማጣራት ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሷል።

ከዚህ በፊት በተሰጠው የ7 ቀን የምርመራ ጊዜ ውስጥ የተጠርጣሪዎችን የጣት አሻራ የማስነሳት ስራ መስራቱን፣ የተጠርጣሪዎችንና የሶስት ሰው ምስክርነት ቃል መቀበሉን፣ ለሲቪል አቪዬሽን፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከኢሚግሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ጤና ኢንስቲትዩት ማስረጃ እንዲሰጠው በደብዳቤ መጠየቁን ገልጿል።

ቀሪ ስራዎች ማለትም ከተቋማት የተጠየቁ ማስረጃዎችንና የሰነድ ትርጉም መቀበልና ተጨማሪ ምስክር ቃል ለመቀበል በወ/መ/ስ/ህ/ቁጥር 59/2 መሰረት የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ ማለትም ወደ ኡጋንዳ ተጎዙ የተባሉት ሁለት ግለሰቦች ወደ ኡጋንዳ መጓዛቸውን አረጋግጠው፤ የተጠቀሰውን ወንጀል አለመፈጸማቸውን ገልጸው ተከራክረዋል።

አራቱ የኢሚግሬሽንና የአየር መንገድ ሰራተኞችም በፖሊስ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ገልጸዋል።

የዋስትና መብታቸው እንዲፈቀድላቸው በጠበቆቻቸው አማካኝነት የጠየቁ ሲሆን÷ በፖሊስ በኩል የዋስትና ጥያቄያቸውን በመቃወም ተከራክሯል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን የተመለከተው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ፖሊስ ቀረኝ ያላቸው ስራዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል በማዘዝ ከተቋማት የሚመጡ ማስረጃዎችን ተጠርጣሪዎቹ ሊያደናቅፉ፣ ማስረጃ ሊያጠፉ አይችሉም የሚለውን ግምት በመያዝ ተጠርጣሪዎቹ ከሀገር እንዳይወጡ እግድ እንዲጣል በማዘዝ ሁለቱ ተጓዦችን በ20 ሺህ ብር ቀሪ የኢሚግሬሽንና የአየር መንገድ ሰራተኞችን ደግሞ በ10 ሺህ ብር ዋስ አሲዘው ከእስር እንዲፈቱ ፈቅዷል።

በዚሁ ጊዜ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ መርማሪ ፖሊስ በመዝገቡ ላይ ይግባኝ ያለ ሲሆን÷ ፍርድ ቤቱም እስከ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ፖሊስ ይግባኝ ማመልከቻ እስኪያቀርብ ዋስትናው ታግዷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.