Fana: At a Speed of Life!

የ2012 ዓ.ም ተሿሚ አምባሳደሮች ስልጠና መስጠት ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን በተለያዩ ሀገራት እንዲወክሉ በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተሾሙት 9 አምባሳደሮች ስልጠና መሰጠት ተጀመረ።
 
ስልጠናውን ያስጀመሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ይህ ስልጠና በውጭ ሀገራት የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የተሾሙ አምባሳደሮች ሀገሪቱ ከምታራምደው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በመነሳት ከወቅታዊው አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ጋር በማዛመድ የሀገሪቱን ተሰሚነት ማጉላትና የህዝቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የራሱ ሚና ስላለው በአግባቡ መከታተልና ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
 
የኢትዮጵያ መሰረታዊ ብሄራዊ ጥቅም ከሀገሪቱ ህልውና፣ ሉዓላዊነት፣ አንድነት፣ ደህንነት እና ክብር ማስጠበቅ እንዲሁም ቀጠይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገትን ከማረጋገጥ ጋር በእጀጉ የተቆራኘ በመሆኑ ይህንን በውል መገንዘብ እና ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ አቶ ገዱ ገልጸዋል።
 
አምባሳደሮቹ በሚወከሉበት ሀገር በሚደረጉ የሁለትዮሽ እና ባለብዙ መድረክ የዲፕሎማሲ ስራዎች ንቁ ተዋናይ በመሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት በትብብር መስራት፣ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስተሮችን የመሳብ፣ ለኢትዮጵያ የወጪ ምርቶች ገበያ የማፈላለግ፣ የሀገሪቱን የቱሪዝም መስህብና ቱባ ባህሎችን የማስተዋወቅ፣ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዜጎችን መብትና ጥቅም በማስጠበቅ ለሀገራቸው የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ የማበረታታትና በቅርበት የመስራት፣ የሳይንስና ቴክኖሊጂ ሽግግርን ለማፈጠን የሚያስቸል መረጃ እና እውቀት ወደ ሀገር ለማስገባት እንዲቻል አምባሳደሮቹ ስልጠናውን ከዚህ ጋር በማዘማድ ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
 
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዓለም በአሁኑ ስዓት በኮቪድ 19 ወርሽኝ በእጅጉ የተጠቃችበት ወቅት በመሆኑ፣ ወረርሽኙን በጋራና በትብብር ለመወጣት የሚያስችሉ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወን ተገቢ መሆኑንም አንስተዋል።
 
ስልጠናው ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 8 ቀናት የሚሰጥ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከጎረቤት ሀገሮች፣ ከአፍሪካ አህጉር፣ ከመካከለኛው ምስራቅ፣ ከኤዥያ ፓስፊክ፣ ከአውሮፓ፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ በውጭ አገር የሚገኙ ዜገቻችን መብትና ለሀገራቸው የሚኖራቸው ሚና፣ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እና መሰል ርዕሶች ላይ ይሰጣል ተብሏል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.