Fana: At a Speed of Life!

የሐረር ቁጥር 4 ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክትን ለማስጀመር እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረር ቁጥር 4 ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክትን ለማስጀመር የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የምስራቅ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ግሪድ ማጠናከሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት የሳይት ተወካይ መኮንን ዓለሙ እንዳሉት÷ ፕሮጀክቱ በሚያርፍበት ቦታ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች ተገቢውን ካሳ ለመክፈል የእርሻ መሬት ልኬትና የተክል ቆጠራ ተከናውኗል፡፡

ይዞታቸው ለፕሮጀክቱ የሚፈለግ 40 የአካባቢው ነዋሪዎች በልኬቱና በቆጠራው መሠረት አስፈላጊውን ካሳ ከፍሎ ለግንባታ ዝግጁ ለማድረግም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

ክልሉና ወረዳው ያዋቀሯቸው ኮሚቴዎች የካሳ ክፍያ ግምቱን አጠናቀው ለተቋሙ እንዲያቀርቡ እና ወደ ሥራ እንዲገባ ከክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ጋር ውይይት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

በቢሮው የከተማ ማደስና መልሶ ማልማት ቡድን መሪ ፈቲ ሁሴን በበኩላቸው÷ የካሳ ክፍያ የመጨረሻ ግምት ጸድቆ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ለአርሶ አደሮቹ ክፍያ የሚፈፀምበት የባንክ ደብተር፣ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ እና ተያያዥ ጉዳዮች እየተጠናቀቁ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የሐረር ቁጥር 4 ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ከሐረር ከተማ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቃሊ ቀበሌ የሚገነባ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ በአፍሪካ ልማት ባንክ ፋይናንስ የሚገነባ ሲሆን÷ የምስራቅ ኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ግሪድ ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.