Fana: At a Speed of Life!

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በወጪ ንግዱ ላይ የፈጠራቸውን አዳዲስ እድሎች ለመጠቀም አማራጭ ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በወጪ ንግዱ ላይ የፈጠራቸውን አዳዲስ እድሎች ለመጠቀም አማራጭ ስትራቴጂ መዘጋጀቱ  ተገለጸ።

ኮቪድ 19 የአለምን መደበኛ እንቅስቃሴ በአዲስ በሚለመድ አዙሪት ውስጥ ከመክተቱም ባለፈ የገቢና የወጪ ንግድ ስርአቱ  አለም አቀፍ ገበያው እና የሚፈለገው ምርት ጭምር ከተለመደው ሁናቴ እየተቀየረ  መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ ።

ከዚያም ባለፈ ወረርሽኙ በጤናው ዘርፍ ላይ ካደረሰው ጉዳት ባልተናነሰ ሁኔታ የሀገራትን  ምጣኔ ሀብትም እየፈተነ ይገኛል።

ኢትዮጵያም ኮቪድ የፈጠራቸው የወጪ ንግድ አማራጮችን የመጠቀም  ስትራቴጂዎችን ነድፋለች።

የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  በነበራቸው የፓርላማ ቆይታ÷ በሽታው አዲስ አበባ መግባቱ እስከተገለጸበት 8 ወር ድረስ በጥሩ አፈጻጸም የተጓዘ ከኮቪድ በኋላም የቡና እና አበባ ምርቶች በገበያው ተፈላጊነት ሽቅብ የወጣበት ነበር ብለዋል ።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ÷ የወጪ  ንግዱ ወረርሽኙ የፈጠራቸውን አዳዲስ እድሎች እየተጠቀመ መሆኑን ተናግረዋል ።

ባለፉት 10 ወራት 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ምርት ለወጪ ገበያው ማቅረብ የተቻለበት እንደመሆኑ በቀጣይም ይህን አለም አቀፍ የገበያ እድሎች የመጠቀም የመውጫ ስትራቴጂ ወይም ኤግዚት ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል  ብለዋል።

ባለፉት 10 ወራት የወጪ ንግዱ 13 በመቶ ጨምሯል ያሉት ሚኒስትሩ ÷ በቀጣይም ምርትን በማሳደግ በአለም አቀፍ ገበያው ውጤታማ ለመሆን ይሰራልም ነው ያሉት ።

ሚኒስትሩ አያይዘውም ካለፈው አመት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር 13 በመቶ የተሻለ  ውጤት  ማስመዝገቡን ተናግረዋል።

በዚህም ዘርፉ በቀጣይ ከኮቪድ 19 ተጽእኖ ተላቆ የገበያ ትሩፋቶችን የማግኘት ቀመር  ተሰልቷል  ብለዋል።

በአውሮፓ እና በአሜሪካ የእንቅስቃሴ ገደቦች መጣል የቡና ምርት ፍላጎቶች እንዲጨምር ማድረጉ ተጠቁሞ÷አሁንም በተለይ ለምግብነት የሚውሉ ምርቶች ተፈላጊ በመሆናቸው የወጪ ንግዱ ቀጣይ ስትራቴጂ ነው ተብሏል።

ኢትዮጵያ ይህን እድል ለመጠቀም በዘላቂነትም ገበያውን ደንበኛ አድርጎ የመቆየት የቤት ስራ ትሰራለችም  ተብሏል።

በሀይለየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.