የጤና ሚኒስቴር በኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ላይ የሚሰሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ወደ ስራ አሰማራ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የጤና ሚኒስቴር በኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ላይ የሚሰሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ወደ ስራ አሰማራ።
ወጣቶቹ “ፕሮጀክት ሆፕ” በተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት አማካኝነት የተሰባሰቡ ሲሆን÷ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለያዩ የትምህርት መስኮች የተመረቁና ለቀጣዩቹ ሶስት ወራት በተለያዩ የጤና ተቋማት ተመድበው አገልግሎት የሚሰጡ ይሆናል።
የጤና ሚኒስትር ድኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ ለበጎ ፈቃደኞቹ የስራ መመሪያ በሰጡበት ወቅት÷ የጤና ባለሙያዎች በሚሰጡት ምላሽ ብቻ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል እንደማይቻል ተናግረዋል።
“የአንድ የበጎ ፈቃደኛ አገልግሎት ዋጋዋ ትልቅ ነው” ያሉት ሚኒስትር ድኤታው÷ ከዚህ አንጻር ዛሬ ወደ ስራ የተሰማሩት ወጣቶች በጤናው ዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን እንደሚሞሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
አያይዘውም በተለይ በኢትዮጵያ የቫይረሱ ስርጭት እየተስፋፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም በተለያዩ መስኮች የሚያገለግሉ በርካታ በጎ ፈቃደኞች ያስፈልጋሉ ብለዋል።
አሁን ላይ የተሰማሩት ወጣቶች 34 ሲሆኑ ንክኪ አሰሳ፣ ሎጀስቲክስ ማጓጓዝ፣ ማሽነሪ ጥገናዎች፣ በጥሪ ማዕከላት ምላሽ መስጠትና ሌሎች ተጓዳኝ ተግባራት ላይ የሚሰሩ ናቸው ተብሏል።
በፕሮጀክቱ አማካኝነት ወጣቶቹ ራሳቸውን ከኮሮናቫይረሱ ጠብቀው እንዴት አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው ስልጠና መሰጠቱንም ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።