ርዕሰ መሥተዳድር ኡሞድ በረመዳን የነበረው መተዛዘን ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠየቁ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በረመዳን ወር ሕዝበ ሙስሊሙ ሲያከናውነው የነበረው ማዕድ የማጋራት፣ የመተጋገዝና የመረዳዳት እሴት ከረመዳን በኋላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ጠየቁ፡፡
አቶ ኡሞድ ለ1 ሺህ 445ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም፥ ሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ አል ፈጥር በዓልን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና ሐይማኖታዊ ሥርዓቱን በመተግበር ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በረመዳን ወር ሕዝበ ሙስሊሙ ማዕድ የማጋራት፣ የመተጋገዝና የመረዳዳት እሴቶችን በተሻለ መልኩ ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁመው፥ ይሄው መተዛዘን ከረመዳን በኋላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብም በክልሉ ሰላምን፣ አብሮነትን፣ መተባበርንና ወንድማማችነትን በማጠናከር የክልሉን ዘላቂ ሰላም እንዲያረጋጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡