Fana: At a Speed of Life!

በጉለሌ ክፍለ ከተማ የተገነባው የተቀናጀ የልማት ስራ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በጉለሌ ክፍለ ከተማ እንጦጦ አካባቢ የተገነባውን የጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራን በዛሬ እለት በማስመረቅ ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ በዋነኛነት በአካባቢው እንጨት ከጫካ በመልቀም ለሚተዳደሩ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ እድል የሚፈጥሩ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጀምረው የተጠናቀቁ የልማት ስራዎች ናቸው ተብሏል፡፡

የጉለሌ የተቀናጀ ልማት በውስጡ ጉለሌ የመኖሪያ መንደርን እንዳካተተ እና የከተማዋን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ለመጨመር በከተማ አስተዳደሩ ወጪ እንደተገነቡ ተገልጿል፡፡

ባለ 5 ወለል አምስት ህንፃዎች፣ 200 አባወራዎችን የሚይዙ፣ ሁሉም ቤቶች ዘመናዊ ሆነው የተሰሩ ሲሆን የመኖሪያ መንደሩ ውብ ምድረ ግቢ አረንጓዴ ስፍራዎች እንዳካተተ በ14 ሺሕ 625 ካሬ ሜትር ላይ እንዳረፈም ተጠቅሷል፡፡

እንዲሁም ጉለሌ እንጀራ ማዕከል ለከተማዋ ሁለተኛው የእንጀራ ፋብሪካ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን÷ በአካባቢው እንጨት በመልቀም ለሚተዳደሩ 551 እናቶች የስራ እድል የፈጠረ ነው ተብሏል፡፡

የእንጀራ ማዕከሉ በውስጡ ሁለት የእንጀራ መጋገሪያ ህንጻዎች፣ የህጻናት ማቆያ፣ የእህል ማከማቻ፣ ወፍጮ እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላትን ያካተተ ነው፡፡

450 ዘመናዊ የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ እንደተገጠመለት፣ ዘመናዊ የሊጥ ማቡኪያ ማሽን፣ ዘመናዊ የአብሲት መጣያ ማሽን፣ ሁለት ወፍጮዎች እና 551 እናቶች በሁለት ፈረቃ ተከፍለው ይሰሩበታልም ነው የተባለው፡፡

በእንጀራ ማዕከሉ ውስጥ የስራ እድል የተፈጠረላቸው እናቶች ከዚህ በፊት በአካባቢው እንጨት በመልቀም ሲተዳደሩ የነበሩ፣ ምንም ገቢ የሌላቸው እና የኑሮ ጫና የበረታባቸው ናቸው፡፡

በአጠቃላይ በ10 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ማዕከል እንደሆነም ከከንቲባ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተጨማሪም ጉለሌ የወተት ማዕከል÷ የወተት ላሞች ሼድ፣ የመኖ ማከማቻ መጋዘን፣ የጥጃ ቤት፣ የሰራተኞች ማረፊያን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከበጎ ፈቃደኛ ባለሃብቶች በተገኘ ድጋፍ 48 የወተት ላሞች ተገዝተው ስራ እንደጀመሩ የተገለጸ ሲሆን÷ በወተት ላሞች እርባታ ላይ ሥራ አጥ የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች በ4 ማሕበራት ተደራጅተው ስራ ጀምረዋል፡፡

የአካባቢውን የመንገድ ትስስር የሚያሳድግ ዘመናዊ 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ግንባታ መከናወኑም ተጠቅሷ፡፡

የዚሁ የጉለሌ የተቀናጀ ልማት ስራ አካል የሆነው ቀጨኔ የተስፋ ብርሃን የቶኩማ ስታር ቢዝነስ ቅርንጫፍ የምገባ ማዕከል ግንባታው ቀድሞ እንዲጠናቀቅ በመደረጉ ቀድሞ ለአካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎት መስጠት የጀመረ ነው፡፡

በአጠቃላይ በዚህ የተቀናጀ የልማት ስራዎች ለ1 ሺህ 533 ነዋሪዎች የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ተብሏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.