ከ235 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ235 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገው ክትትል ነው 169 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የገቢ እና 66 ሚሊየን ብር የወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎች የያዘው፡፡
ከኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሃኒት፣ የመዋቢያ እቃዎች፣አደንዛዥ እጾች፣የመኪና መለዋወጫ፣ የምግብ ዘይት፣ የቁም እንስሳት፣የጦር መሳሪያ እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡
የገቢ እና የወጭ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ቃሊቲ፣ ጅግጅጋ እና ድሬድዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዙ የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
የኮንትሮባንድ እቃዎችን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 13 ተጠርጣሪዎች እና 6 ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተጠቁሟል፡፡