ለተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የነበረው የአምባሳደሮች ስልጠና ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያን በተለያዩ ሃገራት እንዲወክሉ ለተሾሙ አዳዲስ አምባሳደሮች ላለፉት አራት ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ ተገኝተው የመዝጊያ ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸው አምባሳደሮቹ በተለያዩ ሃገራት የኢትጵያን በሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የተወከሉ እንደመሆናቸው የተጣለባቸውን ታላቅ ሃላፊነት የሚመጥን ተጨባጭ እንቅስቃሴ ማከናወን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
አምባሳደሮቹ ከሚመሯቸው የሚሲዮን ሰራተኞች፣ ከዋናው መስሪያ ቤት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የቅርብ ግንጘኑነትና ጥብቅ ትስስር በመፍጠር እንዲሁም ለዚሁ የሚያግዝ ትክክለኛ እቅድ በማዘጋጀትና ይህንኑ መሰረት አድርጎ መንቀሳቀስ እሰፈላጊ እንደሚሆን አቶ ገዱ ገልጸዋል።
እንደየተመደቡበት ሃገር ተጨባጭ ሁኔታ የሃገራቸንን ትክክለኛ ገጽታ በአዎንታዊ በመገንባት ባለህባቶችን የመሳብ፣ አስጎብኚ ድርጅቶችን የማግባባት፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ምርቶች ተገቢውን ገበያ የማፈላለግ ቁልፍ ስራ ላይ በማተኮር ውጤት ማስመዝገብ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አቶ ገዱ በአጽንኦት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትጵያውያን ራሳቸውን ጠቅመው ለሃገራቸውም የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ አምባሳደሮቹ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው በማሳሳብ በሚሄዱበት ሃገር ሁሉ መልካም የስራ ጊዜ እንዲሆንላችው ተመኝተዋል።
በመዝጊያ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰው ሀብትና አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው ከዘርፉ አንጻር አምባሳደሮቹ በሚወከሉባቸው ሃገራት ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ ማድረጋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።