ሚኒስቴሩ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር በጋራ በሚሠራባቸው ዘርፎች ላይ ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሃሰን እንደ ተቋም በጋራ በሚሠሩ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ፡፡
በውይይታቸውም በክልሉ ያለውን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት በማልማት ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በክኅሎት፣ ቴክኖሎጂ ልማት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና ተያያዥ ጉዳዮች ትኩረት በሚሹ ሥራዎች ላይ መምከራቸውን ሚኒስትሯ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
በዚህም የእሴት ሰንሰለትን መሰረት ያደረገው ክኅሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ አቅጣጫችን እሴት አካይ ድጋፍና ክትትል እንደሚያስፈልገው እና ችግር ፈቺ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ወደ ሕብረተሰቡ ማድረስ እንደሚያስፈልግ የጋራ ሐሳብ ይዘናል ብለዋል፡፡
እንዲሁም በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዓለም አቀፍ እውቅና ባገኘው የብየዳ ማዕከል በልዩ የክረምት ወራት የቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ እና የፈጠራ ሐሳቦች ማሻሻያ መርሐ-ግብር እየተሠሩ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን መጎብኘታቸውንም አመላክተዋል፡፡
በጉብኝታቸውም በክልሉ ያሉ የተፈጥሮ ፀጋዎችን በአግባቡ አልምቶ ከመጠቀም ባለፈ ተኪ ምርቶች ላይ ሀገራዊ አቅም ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ ጥረቶች እና ውጤቶች አበረታች መሆናቸውን ተመልክተናል ብለዋል፡፡
አቶ አሻድሊ ከሚኒስቴሩ ጋር በረጋራ ለመሥራት ላሰዩት ቁርጠኝነትም ሚኒስትሯ አመስግነዋል፡፡