Fana: At a Speed of Life!

ከበጋ መስኖ ስንዴ እስከ አሁን ከ 90 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)ከበጋ መስኖ ስንዴ እስካሁን ከ90 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)ገለጹ፡፡

ግብርና ሚኒስቴር የ2016 በጀት አመት ያለፉትን 10 ወራት የስራ አፈጻጸም የገመገመ ሲሆን ÷ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ያለፉት 10 ወራት በግብርናው ዘርፍ በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በበጀት አመቱ 3 ሚሊየን ሔክታር መሬትን በመስኖ ስንዴ በማልማት 120 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ባለፉት 10 ወራት ብቻ 2 ነጥብ 97 ሚሊየን ሔክታር መሬትን በዘር በመሸፈን ከ90 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የመስኖ ስንዴው ተሰብስቦ አለመጠናቀቁን የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ ቀሪውንም ለመሰብሰብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።፡

ከሌማት ትሩፋት አንጻር አጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ከእቅድ በላይ አፈጻጸም የተስተዋለበት መሆኑን አመላክተው በበጀት ዓመቱም እስካሁን 57 ሚሊየን ጫጩቶችን ማስፈልፈል መቻሉን ለአብነት አንስተዋል፡፡

ህዝብን ያሳተፈ የተፋሰስ ስራ በመስራትም የአፈር ክለት መጠንን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ መቻሉን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) አክለውም ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን ለማፍላት ታቅዶ እንደነበር አውስተው፤ ነገርግን ከእቅድ በላይ 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን ማፍላት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮው የበልግ ወቅት 3 ነጥብ 1 ሚሊየን ሔክታር መሬት በዘር ለመሸፈን መታቀዱ እና እስካሁን ድረስ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑም ተመልክቷል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.