መንግስት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ቁርጠኛ ነው – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ለማጠናከር፣ ልማትን ለማፋጠን፣ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መንግስት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ አደም ፋራህ ገለጹ።
መንግሥት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጣይነት ምክክር የሚደረግባቸውን ሀገራዊ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ለመወሰን የሚያስችል የምክክር መድረክ አካሂደዋል።
በመድረኩ የተገኙት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ አደም ፋራህ÷ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ሀገራዊና ችግር ፈቺ አጀንዳዎችን በመለየት ቀጣይነት ያለው ውይይት እንዲደረግ አቅጣጫ አስቀምጠው እንደነበር አውስተዋል።
አጀንዳ ለመለየት የመጀመሪያ በሆነው በዛሬው መድረክ መንግሥትና ሀገራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩና እስከ ክልል ድረስ በሚደረጉ ውይይቶች ትኩረት የሚደረግባቸው የጤናማ ፉክክርና የትብብር አጀንዳዎች መለየታቸውን ገልፀዋል።
ጤናማ የፖለቲካ ፉክክር እንዲኖር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ ፓርቲዎች ከመንግሥት የሚፈልጓቸው ድጋፎች፣ የፖለቲካ ምህዳሩን የሚጎዱ ምክንያቶች፣ የሚዲያ አጠቃቀም እና የምርጫ ጉዳይ ተካተዋል።
ሁለተኛው ዘርፍ ሀገራዊ ትብብር ሲሆን የሰላምና ፀጥታ፣ ፍትሕና ሰብዓዊ መብት፣ ማክሮ ኢኮኖሚ፣ ዲፕሎማሲ፣ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥና መልካም አስተዳደር፣ አካታች ሀገራዊ ምክክር እንዲሁም ማንነትና ሀገራዊ ትስስርን ባካተተ መልኩ ምክክር እንዲደረግባቸው መግባባት ላይ መደረሱን ገልፀዋል።
ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር፣ ከዚያ መለስ ያሉ ጉዳዮች ከፌደራል ተቋማት አመራሮች እንዲሁም የክልል ጉዳዮች ከክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጋር እንዲመከርባቸው አቅጣጫ መቀመጡን ይፋ አድርገዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አጀንዳዎቹን ካደራጀ በኋላ ከአጀንዳው ባህሪ እና ወቅታዊነት አንፃር በቅደም ተከተል ውይይት እንዲደረግ መግባባት ላይ መደረሱን አንስተዋል።
መንግሥት ለፖለቲካዊ ምህዳር መስፋት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አንስተው፤ ሁሉም የመንግስት መዋቅር ለምህዳሩ መስፋት ሕግን አክብሮ እንዲሰራ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሕግና መርህ መገዛት እንዳለባቸውና ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ የልማትና ደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።
ኢትዮጵያን ከግጭት አዙሪት በማውጣት ዘላቂ ሠላም ለመገንባት መንግሥት እየወሰዳቸው ላሉ የሰላምና የሕግ ማስከበር እርምጃዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች አጋዥ እንዲሆኑም ጠይቀዋል።
የትኛውንም ችግር በሰላማዊ መንገድ መፍታት የመንግሥት ቀዳሚ ትኩረት መሆኑን ያነሱት አቶ አደም፤ የትጥቅ አማራጭን የተከተሉ ኃይሎች ከመንግሥት ጋር በሰላማዊ መንገድ እንዲነጋገሩ ፓርቲዎች ማገዝ አለባቸው ብለዋል።
መንግሥት ሰላማዊ ውይይትን አጥብቆ የመፈለጉን ያህል በኃይል የሀገርና የህዝብ ደህንነትን የሚያውኩ አካላትን ስርዓት የማስያዝ ህጋዊ ግዴታ እንዳለበት መገንዘብ ይገባልም ነው ያሉት።
በውይይቱ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስቀመጡትን አቅጣጫ ለመተግበር መንግሥት ቀዳሚውን እርምጃ መጀመሩን አድንቀዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ መለሰ ዓለሙ፤ በውይይቱ ሀገራዊ የሰላምና ፀጥታ እንዲሁም የኢኮኖሚ አጀንዳዎች ላይ ተከታታይ ውይይት ለማድረግ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ፤ ውይይቱ የፖለቲካ ባህላችንን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር መሰረት የሚጥል እና ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አጀንዳዎች የተነሱበት ነው ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትም ዛሬ የተነሱ አጀንዳዎችን የማደራጀት ኃላፊነት መውሰዱን መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ የመንግሥት ተጠሪ ነቢሃ መሐመድ፤ የዛሬው ውይይት የጋራ አጀንዳዎች የተለዩበት እና ለሀገሪቱ ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ምክትል መሪ ዮሐንስ መኮንን፤ አንገብጋቢና ስትራቴጂካዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመምከር መግባባት እንደተፈጠረ ጠቅሰው፤ እንዲህ ያሉ መድረኮች መለመድ አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ ራሔል ባፌ፤ በውይይቱ ከተለዩ አጀንዳዎች መካከል የሀገራዊ ምክክሩ አንደኛው ነው ብለዋል።
በመሆኑም በቀጣይ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና መንግስት ለሀገራዊ ምክክሩ፣ ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ደኅንነትና ሌሎችም ጉዳዮች የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።