ሚኒስትር ዴዔታ ሰመሪታ ከሳዑዲ የገንዘብ ፖሊሲና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ም/ሚኒስትር ጋር መከሩ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ሰመሪታ ሰዋሰው ከሳዑዲ ዓረቢያ የገንዘብ ፖሊሲና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ምክትል ሚኒስትር አብድልሙሁሴን አልከሊፍ ጋር ተወያዩ።
በውይይታቸውም ሳዑዲ ዓረቢያ ለኢትዮጵያ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ በመሰረተ-ልማት ግንባታዎች እያደረገች ላለችው የልማት ትብብር ሚኒስትር ዴዔታዋ አመስግነዋል፡፡
ሀገራቱ ካላቸው የመልከዓ-ምድር አቀማመጥና የባህል ቅርርብ አንፃር ሰፊ የትብብር መስክ አማራጮች እንዳሉም አመላክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ካለው የኢኮኖሚ አቅም ባሻገር በተለያዩ መስኮች እየተወሰደ ያለውን ሪፎርም እንደ መልካም ዕድል በመጠቀም የትብብር መስኮችን ማስፋት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ምክትል ሚኒስትሩ በበኩላቸው÷ በሳዑዲ በኩል በኢትዮጵያ እየተፈጠረ ያለውን የኢንቨንስትመት አማራጭ ለመጠቀም ያለውን ፍላጎት መግለፃቸውን በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል፡፡
በዓለም ዓቀፍ መድረኮች ለኢትዮጵያ ድምፅ በመሆን በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለውን የልማት ዕቅድ ድጋፍ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል፡፡