Fana: At a Speed of Life!

ይህ የምክር ምዕራፍ በቀጣዩ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ምክክር የሚደረገባቸውን መሠረታዊ ጉዳዮች ለመለየቱ ስራ ቁልፍ ሚና አለው – መስፍን አርዓያ(ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የከተማ አስተዳደርና ክልላዊ የምክክር ምዕራፍ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ተጀምሯል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ÷ ኮሚሽኑ በምሁራን ፣ልሂቃንና በተለያዩ የፖለቲካ ተቋማት ጥያቄ የመንግስት ፈቃድና ፍላጎት ታክሎበት በ11 ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች በሚገባ ተቃኝቶ መቋቋሙን አውስተዋል፡፡

የተደራጁ የሃይማኖት፣ የሲቪል ማህበረሰብ እና የፖለቲካ ተቋምትን በየደረጃው በማካተት በ4 ምዕራፍ በከፋፈላቸው የሥራ መርሐ ግብሮቹ ውስጥ ሁለቱን በማጠናቀቅ ወደ ሶስተኛው መርሐ ግብር ማለትም የምክክር ምዕራፍ በመሸጋገር ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

በዚህ የምክክር ሒደት ተሳታፊ የሚሆኑት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሃሳብ እና የፖለቲካ መሪዎች እንዲሆኑ በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ በግልፅ መደንገጉንም ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ እነዚህን መሰረታዊ ሃሳቦች መነሻ በማድረግ ተሳታፊዎችን የመለየት ስራውን አሳታፊና አካታች በሆነ መንገድ ለማከናውን አስፈላጊ የሆኑ ተግባራትን በጥንቃቄ ሲያከናውን መቆየቱን ገልፀዋል፡፡

በዚህ መልኩ የተለዩ ተወካዮች በሒደቱ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ከሚያደርጉባቸው ምዕራፎች መካከል ዋነኛ የሆነውን የምክክር አጀንዳዎችን የመለየት ሒደት ዛሬ በይፋ እንደሚጀመርም አስታውቀዋል፡፡

“ይህ የምክክር ምዕራፍ ነው የምንልበት ምክንያት በቀጣይ በሚካሄደው ሀገራዊ ጉባዔ ምክክር የሚደረገባቸውን እጅግ መሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች አሳታፊና አካታች በሆነ ሂደት የመለየቱ ስራ በራሱ ምክክር የሚፈልግና መግባባትን የሚጠይቅ በመሆኑ ነው፡፡ ” ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ከመዲናዋ 119 ወረዳዎች የተወጣጡ ተሳታፊዎች ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች የሚወክሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም አዲስ ውጤት ለማግኘት በአዲስ መንገድ መሄድ አስፈላጊ እንደመሆኑ ኮሚሽኑ ህዝቡ በተወካዮቹ አማካኝነት ትርጉም ያለው ተሳትፎ በማድረግ ስር የሰደዱ ችግሮችን ምንጭ ከመለየት ጀምሮ በምክክር ሒደቱ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት እኩል የመሳተፍን ታሪካዊ መድረክ መፍጠሩን አውስተዋል፡፡

ይህን ታላቅና ታሪካዊ ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት መቻል በኢትዮጵያ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል እንዲሁም በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻልና መተማመን የሰፈነበት አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል፡፡

ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮቻችንን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ባህል ለማዳበር ብሎም ወደ እልቂት የማንገባበትን ሁኔታ ለመፍጠር ያስችላል ተብሎ እንደሚታመንም ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም ወቅታዊ ችግሮቻችን ዘላቂ በሆነ መንገድ በመፍታት ሰላማችንን አስተማማኝ በሆነ መሠረት ለማቆም እንዲሁም ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመገንባት የሚደረገው ጥረት በስኬት እንዲቋጭ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡

በዚህም ህዝቡ በተወካዮቹ አማካኝነት ትርጉም ያለው ተሳትፎ በማድረግ ስር ለሰደደው ሀገራዊ ችግር መፍትሄ እንዲገኝና ምክክሩ በስኬት እንዲቋጭ ሁሉም የበኩሉን ሃላፊነት እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.