በኢትዮጵያ 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ቶን ካርበን መከማቸቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከመጨመሩም በላይ 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ቶን ካርበን ማከማቸት መቻሉን የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ፡፡
ባለሥልጣኑ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በአካባቢ ቀን አከባበር ዙሪያ በሰጠው መግለጫ÷ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ሥራ ከሀገር አልፎ በዓለም የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ ጉልህ ድርሻ እየተወጣ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር የተከናወኑ የደን ማልማት ሥራዎች በአየር ንብረት ሥርዓቱ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማማስመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከመጨመሩም በላይ 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ቶን ካርበን ማከማቸት መቻሉን ገልጸው÷ ይህም ከሀገር አልፎ ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ሥነ-ምኅዳር ጉልህ ድርሻ እንዲያበረክት አድርጓል ብለዋል፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ለሊሴ ነሜ (ኢ/ር) በበኩላቸው÷ የፊታችን ግንቦት 27 እና 28 በሀገር አቀፍ ደረጃ “የመሬት ማገገም በርሀማነትን እና ድርቅን መቋቋም” በሚል መሪ ሐሳብ የአካባቢ ቀን በተለያዩ መርሐ-ግብሮች እንደሚከበር አስታውቀዋል፡፡
የበዓሉ አከባበርም ከኢትዮጵያ ደን ልማት እና ከአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በቅንጅት እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡
በሰሎሞን ይታየው