የውጭ ሀገር ህጋዊ የሥራ ስምሪትን ወደ አውሮፓና እስያ ለማስፋት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ሀገር ህጋዊ የሥራ ስምሪትን ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በተጨማሪ ወደ አውሮፓና እስያ ሀገራት ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
ከሀገራት ጋር ህጋዊ የሥራ ስምሪት ስምምነት በማድረግ የሰለጠነ የሰው ሃይል ስምሪት እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት የዜጎችን መብት፣ ክብርና ደኅንነት በማስጠበቅ የተሻለ ክፍያና የአሰሪ ግንኙነት እንዲፈጠር መደረጉንም ተናግረዋል።
በ10 ወራት 304 ሺህ ዜጎች ስምምነት ወደተደረሰባቸው ሀገራት የሥራ ስምሪት ማድረጋቸውን ገልጸው፤ በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ከመካከለኛው ምስራቅ በተጨማሪ ወደ አውሮፓና እስያ ገበያም እየተገባ መሆኑን ጠቁመዋል።
በየሀገራቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ለዜጎች የቅርብ ድጋፍና ክትትል እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር እየተሰራ ነው ብለዋል።
የስራ ስምሪት ህጋዊ ስምምነት ባልተደረገባቸው ሀገራት “ለሥራ እንልካለን” የሚሉ ህገ-ወጥ አዘዋዋሪና አጭበርባሪዎች በመኖራቸው ዜጎች እንዳይታለሉ መምከራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በዚህ ህገ ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት ላይ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ዜጎችም ለሚኒስቴሩና ለህግ አስከባሪ አካላት ጥቆማ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
ዜጎች በተቋሙ የማህበራዊ የትስስር ገጽ ላይ በመግባት ህጋዊ የሥራ ስምሪት ሰጪ ኤጀንሲና ተቀባይ ሀገራትን በማረጋገጥ ከህገወጥ አዘዋዋሪዎች እራሳቸውን እንዲጠብቁም አስገንዝበዋል።