Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል የህግ የበላይነትን በማስከበር፣ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ከጎበኙ በኋላ ከክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ አቶ ሽመልስ አብዲሳ÷ የክልሉ መንግስት ድህነትን ለማሸነፍ፣ ዴሞክራሲን ለማጽናትና የህግ የበላይነትን ለማስከበር በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት የጋራ ጥረትና የረጅም ጊዜ ትግል የሚፈልግ መሆኑን ገልጸው÷ ሁላችንም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ሳንታክት መስራት አለብን ብለዋል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፏቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የክልሉ መንግስት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከየትኛውም አካል ጋር በሰላማዊ መንገድ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርብ መቆየቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይም በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀስ አካል ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተሻለ ሰላም መኖሩን ገልጸው፤ ይህ ሰላም እንዲመጣ ህዝቡ ከመንግስት ጋር በቅርበት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በበኩላቸው፤ ብልፅግና ፓርቲ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ከሰላምና ጸጥታ ጋር በተያያዘ ችግሩን በአግባቡ መረዳትና ለመፍትሄውም በጋራ መስራት እንደሚገባ ማስረዳታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከጨፌ ኦሮሚያ ጀምሮ የሰላማዊ ትግል ጥሪ ሲቀርብ መቆየቱን አስታውሰው፤ አሁንም ሰላም እንዲሰፍን በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.