የኢትዮጵያና የኮሪያ ሪፐብሊክ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ የሚጠናከርበት ስምምነት ተደርጓል – አቶ አህመድ ሺዴ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያና የኮሪያ ሪፐብሊክ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ የሚጠናከርበት ስምምነት መደረጉን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ደቡብ ኮሪያ ሴኡል ገብተዋል።
በቆይታቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሚኒስትሮች ልዑካን ጋር በመሆን በኮሪያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ይሳተፋሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ይኦል ጋር ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት የኢትዮጵያና የኮሪያ ሪፐብሊክ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መነጋገራቸውን አቶ አህመድ ሺዴ በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል።
የኮሪያ ሪፐብሊክ መንግስት ለኢትዮጵያ ልማት የፋይናንስ እገዛ ማድረግን ጨምሮ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነትን ማጠናከር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና ግብርና ልማት ዙሪያ ይበልጥ ተቀራርበው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል ብለዋል።
ከመሪዎቹ ውይይት በኋላም ለአራት አመታት የሚተገበር የ1 ቢሊየን ዶላር የልማት ፋይናንስ ትብብር ስምምነት መፈረሙን ተናግረዋል።
በተደረሰው ስምምነት መሰረትም ገንዘቡ ለመሰረተ ልማት፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ፣ ለጤና እና የከተማ ልማት የሚውል ይሆናል ብለዋል።
የፋይናንስ ልማት ትብብር ስምምነቱ የሀገራቱን ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረው፤ የአሁኑ የልማት ፋይናንስ ትብብር ስምምነት የኮሪያ ሪፐብሊክ መንግስት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን እገዛ ማጠናከሩን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኮሪያ ሪፐብሊክ አሁን ከደረሰችበት ዕድገት አንጻር ኢትዮጵያ በርካታ ልምድ እንደምትቀስም ገልጸው፤ ከዚህ በፊት የተወሰደውን ልምድ ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል ንግግር በመሪዎቹ መካከል መደረጉን ጠቁመዋል።
ኮሪያ ሪፐብሊክ በቴክኖሎጂና በኢኮኖሚ ያላትን ልምድ ለማካፈል ያላትን ተሞክሮ ለኢትዮጵያ እንደምታጋራ ማረጋገጧን ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ልዑካቸው ጉብኝት ታሪካዊውን የኢትዮጵያና የኮሪያ ሪፐብሊክ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው ያሉት ደግሞ በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ናቸው።
የነበረው ጉብኝት ያለንን ታሪካዊ ግንኙነት የሚያጎላና በቀጣይ አዳዲስ ትብብሮችና ግንኙነቶች መንገድ የሚከፍት ነው ሲሉ ገልጸዋል።