Fana: At a Speed of Life!

ም/ጠ/ሚ ተመስገን ከተረጂነት እንውጣ የሚል አብዮት መቀስቀስ አለብን አሉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከተረጂነት እንውጣ የሚል አብዮት መቀስቀስ አለብን ሲሉ አስገነዘቡ፡፡

ተፈጥሯዊም ይሁን ሰው ሰራሽ አደጋ አይቀሬ ነው ያሉት አቶ ተመስገን፤ ለዚህ ደግሞ አደጋን በራስ አቅም የማስተዳደር እና የመሸከም አቅምን ማጎልበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ዛሬ ባደረግነው የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባም÷ በአዲስ መልክ የፀደቀውን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲ ማስፈንጠሪያዎችና የትግበራ ጉዳዮች ላይ ተወያይተናል ብለዋል፡፡

እንዲሁም የ2016 በጀት ዓመት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ዕቅድ አፈጻጸምን ገምግመናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የአደጋ ስጋት ስራዎች በሙሉ አቅም ለመፈፀም የባህል ለውጥ ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህን የባህል ለውጥ ለማምጣት ደግሞ ልመናን የሚፀየፍ ትውልድን መፍጠር፣ የቆየውን የመደጋገፍና የመረዳዳት ማህበራዊ ዕሴት በማጠናከር እና በማጎልበት ራስን መቻል ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

በዓድዋ ጊዜ የነበረንን የአርበኝነት ወኔ እና ተነሳሽነት ድህነትን ለማሸነፍ መጠቀም ይኖርብናል፤ ለዚህ ደግሞ እንደ ሀገር የጀመርናቸውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማቶች ማፋጠን ወሳኝ ነው ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ዋናው ጠላታችን የሆነውን ድህነትና ኋላቀርነትን ማሸነፍ ለነገ የማይባል ተግባር ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡

የአደጋ ስጋት ስራ አመራር የአንድ ወገን ስራ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንስ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በጋራ አሳታፊ በማድረግ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት አመላክተዋል።

በሌላ በኩል ይሄን ቅንጅታዊ አሰራር በቴክኖሎጂ በመደገፍ የመረጃ ጥራትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው÷ ይህ ደግሞ ውሳኔዎችን በተገቢው መንገድ ለማሳለፍ በዕጅጉ ይጠቅማል ነው ያሉት፡፡

በቀጣይም የማይመጥነን የተረጂነትና የጠባቂነት አስተሳሰብ ክብረ-ነክ፣ ነፃነትን የሚያሳጣና የሉዓላዊነት ሳንካ መሆኑን በመረዳት ከአመራር እስከ ዜጋ መግባባት በመፍጠር የጀመርነውን አብዮት ለማስቀጠል ከስምምነት ላይ ደርሰናል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.