ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ከተረጅነት ባህል መውጣት ይገባል – ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ከተረጅነት ባህል መውጣት ይገባል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ፡፡
‘ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነት እና ክብር’ በሚል መሪ ሃሳብ ከጎንደር ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
በዚሁ ወቅት ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) እንደገለጹት÷ በኢትዮጵያ ስር ሰዶ የቆየውን የተረጂነት አስተሳሰብ ማስወገድ ያስፈልጋል።
ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የራሳችን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ልመናንና ተረጂነትን የሚፀየፍ ማህበረሰብ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ በበኩላቸው÷ በከተሞች እድገት ታሪክ የራሷ ጉልህ አሻራ ያላት ጎንደር በራሷና በዙሪያዋ በርካታ የቱሪዝም መስህቦች ባለቤት እንዲሁም ትልቅ የመልማት እድልና አቅም ያላት ከተማም መሆኗን አንስተዋል፡፡
በምናለ አየነው