ማየትና መስማት የተሳናቸው ዜጎችን ተጠቃሚነት ለማጠናከር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ማየትና መስማት የተሳናቸው ዜጎችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማጠናከር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል አለ የኢትዮጵያ ማየትና መስማት የተሳናቸው ብሄራዊ ማህበር፡፡
ማህበሩ ማየትና መስማት የተሳናቸው የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያለመ የበጎ ፈቃደኞች አምባሳደርና አማካሪ ሹመት አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት አካሂዷል፡፡
በዚህ ወቅትም ማየትና መስማት የተሳናቸው ዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እና በሁሉም ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ማየትና መስማት የተሳናቸው ብሄራዊ ማህበር የፕሮጀክት ኦፊሰር አቶ መሳይ እንደሚሉት÷ ማየትና መስማት የተሳናቸው ዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው፡፡
ማየትና መስማት የተሳናቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ልክ እንደሌሎች ዜጎች እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከግንዛቤ ማነስ ጋር ተያይዞ ማየትና መስማት የተሳናቸው ዜጎችን በተለያዩ ዘርፎች እኩል የማሳተፍ ውስንነት እንደሚስተዋል አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
መሰል ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም ማህበሩ የአምባሳደር ሹመት የሰጣቸው በጎ ፈቃደኞች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡
አምባሳደሮቹ ማየትና መስማት የተሳናቸው ዜጎች በርካታ ክህሎት ያላቸው እና ከሌሎች ዜጎች ጋር እኩል መሳተፍ እንደሚችሉ ለማህበረሰቡ ለማስገንዘብ እንደሚሰሩ አመልክተዋል፡፡
እንዲሁም ማየትና መስማት በተሳናቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የሚፈጠሩ ተግዳሮቶችን ለሚመለከታቸው አካላት በማሳወቅ እንዲፈቱ ጥረት እንደሚያደርጉ ጠቅሰዋል፡፡
በተለይም ማየትና መስማት የተሳናቸው ወገኖች መብት እንዲከበር እንዲሁም የትምህርት፣ የሥራ፣ የሥልጠና እና ሌሎች እድሎችን እንዲያገኙ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል በተለያዩ ዘርፎች ተመርቀው ሥራ ያላገኙ ማየትና መስማት የተሳናቸው ዜጎች የክህሎት ሥልጠና በመስጠት የስራ እድል ለመፍጠር መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ለዚህም የመንግሥትና የግል ተቋማት ክፍት የሥራ ቦታ ሲኖር ማየትና መስማት ለተሳናቸው ወገኖች በቂ እድል መስጠት እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡
የኢትዮጵያ ማየትና መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር ማየትና መስማት የተሳናቸው ዜጎች ተወዳዳሪ አቅም እንዲፈጥሩ፣ መብትና ግዴታቸውን እንዲከበር፣ በየዘርፉ በተደራጀ አግባብ ሁለገብ አቅማቸውን በማጎልበት የዜግነት መብታቸው ተጠብቆ በሃገሪቱ በወጡ ፖሊሲዎች፣ በተነደፉ የአፈጻጸም ስትራቴጂዎች፣ በተዘረጉ ልማት ፕሮግራሞችና ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ከሌሎች ዜጎች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በትጋት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ማህበር ነው፡፡
http://ማየትና መስማት የተሳናቸው ዜጎችን ተጠቃሚነት ለማጠናከር