Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ከተማ ህዝባዊ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ጋምቤላ ከተማ ‘ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነት እና ክብር’ በሚል መሪ ሀሳብ ህዝባዊ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

በውይይቱ ላይ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ፣ የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባልና የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ሚኒስትር አቶ መለሠ ዓለሙ፣ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ጁል ናንጋልን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችም ተገኝተዋል።

ኋላ ቀር አስተሳሰብና ግጭት ለሀገራዊ ምርትና ምርታማነት ጉዞ እንቅፋት መሆኑን በመድረኩ የተናገሩት አቶ ገብረመስቀል ጫላ፤ እንደ ሀገር የገጠሙን ሁሉን አቀፍ ችግሮችና የሰላም እጦት ለምርትና ምርታመነት ጉዟችን እክል ሆነዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት 30 እና 40 ዓመታት ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ በማውጣት ስንዴ ስትገዛ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ይህን ታሪክ አድርገናል ሲሉ ገልጸዋል።

በዚህ የተገኘውን ልምድ በሌሎች ላይ ለመድገም በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ርብርብ ማስቀጠልም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በጋምቤላ ክልል ሰፊ የመልማት አቅም ያለው መሬት እና ይህንን ሊያለማ የሚችል የውሃ ሃብት መኖሩን ገልጸው፤ ይህንን በማስተሳሰር ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ዜጎች የተረጅነት አስተሳሰባቸውን በመቅረፍም በራስ አቅም አምርቶ መብላትን በመለማመድ የተረጂነት ስምን መፋቅ እንደሚገባ በመድረኩ ተነስቷል።

በአሸብር ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.