በሕገ-ወጥ መንገድ ከ92 ሺህ ዶላር በላይ ደብቆ የተያዘው ተጠርጣሪ ተከሰሰ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕገ ወጥ መንገድ ከ92 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ በተሽከርካሪ ውስጥ ደብቆ ተይዟል የተባለው ግለሰብ ላይ ክስ ተመሰረተ።
የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ ምስራቅ ሸዋ ዞን ምድብ ዐቃቤ ሕግ አብዱላዚዝ አደም ሙሐመድ ላይ የብሔራዊ ባንክ አዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀጽ 26 ስር የተመላከቱ ድንጋጌዎችን ጠቅሶ ዝርዝር ክስ አቅርቦበታል።
በክሱ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው ፥ ተከሳሹ በግንቦት 13 ቀን 2016 በኦሮሚያ ክልል መተሀራ ከተማ ፈንታሌ ወረዳ በገልቻ ቀበሌ የተሳቢ ተሽከርካሪ ዳሽ ቦርድ ስር 92 ሺህ 300 ዶላር ደብቆ ሲንቀሳቀስ በፀጥታ አካላት በተደረገበት ፍተሻ በቁጥጥር ስር የዋለ መሆኑ ተጠቅሶ ክስ ቀርቦበታል።
ዐቃቤ ሕግ የክሱን ዝርዝር ለኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎትም አቅርቧል።
ተከሳሹም ችሎት ቀርቦ የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሰው ተደርጓል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ ማስረጃ መርምሮ በቀጣይ ቀጠሮ የሚሰጠውን ውሳኔ የምናቀርብ ይሆናል።
በታሪክ አዱኛ