የፀረ-ተኅዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ በሽታን ለመከላከል እንቅፋት ሆኗል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፀረ-ተኅዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ ተላላፊ በሽታወችን ለመከላከል በሚሠራው ሥራ ላይ አሥቸጋሪ ሁኔታ መፍጠራቸው ተመላከተ፡፡
ጤና ሚኒስቴር፣ ግብርና ሚኒስቴር እና የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ከአጋር አካላት ጋር ሆነው 12ኛውን ሀገር አቀፍ የፀረ-ተኅዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ቀንን አክብረዋል፡፡
በዚሁ ወቅትም በፀረ-ተኅዋስያን መድኃኒቶች ላይ ያለው አጠቃቀም አግባብነት የጎደለው መሆኑና በበሽታ አምጭ ተኅዋስያኑ በቀላሉ እንዲለመዱ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
በተለይም ከጤና ባለሙያ ትዕዛዝ ውጭ መወሠዳቸው እና የታዘዘን የፀረ-ተኅዋስያን መድኃኒት ማቋረጥ ለችግሩ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡
ይህም እንደ ሀገር እየተከሰቱ ላሉ ወረርሽኞች ምክንያት መሆኑ የተመላከተ ሲሆን÷ ይህንን ችግር ለመከላከል እና የፀረ-ተኅዋስያን መድኃኒቶችን የመከላከል አቅም ለማሣደግ ከአጋር አካላት ጋር መሥራት ይገባል ተብሏል፡፡
የፀረ-ተኅዋስያን መድኃኒቶችን በአግባቡ በመጠቀም እንደ ሀገር የሚደርሰውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት መመከትም እንደሚገባም ነው የተመላከተው፡፡
በሰሎሞን ይታየው