አቶ ኦርዲን የጤና ኮሪደር ሥራው የሜዲካል ቱሪዝሙን ያጎለብተዋል አሉ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረር ከተማ እየተገነባ ያለው የጤና ኮሪደር ሥራ የሜዲካል ቱሪዝሙን በይበልጥ ያጎለብተዋል ሲሉ ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
አቶ ኦርዲን በሐረር ከተማ እየተገነባ ያለውን የጤና ኮሪደር ልማት ሥራ በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት÷ በከተማዋ ከአጂፕ እስከ ደከር የጤና ኮሪደር በመገንባት ያለውን የሜዲካል ቱሪዝም በይበልጥ ለማጠናከር እየተሠራ ነው፡፡
በክልሉ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የጤና ኮሪደር ልማት መንገዱን ቀድሞ ከነበረበት 7 ሜትር ስፋት ወደ 30 ሜትር በማስፋት ግንባታው እየተካሄደ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
መንገዱ የተሽከርካሪ፣ ብስክሌት እና የእግረኛ መንገድን በማካተት የስማርት ሲቲ ሞቢሊቲ ጽንሰ-ሐሳብን ባማከለ መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝም ነው ያስረዱት፡፡
የኮሪደር ልማት ሥራው በአካባቢው የሚገኙ የተለያዩ የግል እና የመንግሥት የጤና ተቋማትን እርስ በርስ እንደሚያገናኝም አረጋግጠዋል፡፡
በቀጣይም በጤናው ዘርፍ ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሀብቶች በኮሪደሩ ላይ የመስሪያ ቦታ ይመቻችላቸዋል ብለዋል፡፡
የጤና ኮሪደር ልማቱ በርካታ የጤና ተቋማትን ያቀፈ መሆኑ ዜጎች አማራጭ ኖሯቸው ለተጨማሪ ወጪ እና እንግልት ሳይዳረጉ የፈለጉትን አገልግሎት በአንድ አካባቢ እንዲያገኙ ያስችላል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም በጤና ተቋማት መካከል ጤናማ የሆነ ውድድርና ትብብር እንዲኖር በማስቻል የጤና ተቋማቱ የተሻለ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ የሜዲካል ቱሪዝሙን በይበልጥ እንደሚያቃቃውም አስገንዝበዋል፡፡