ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን አሶሳ ገቡ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የልማት ሥራዎችን ለመጎብኘት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ገብተዋል፡፡
አሶሳ ከተማ ሲደርሱም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሃሰንን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የከተማዋ ነዋሪዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የማዕድን ሚኒስትር ሐብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) እና ሌሎች የፌደራል የሥራ ኃላፊዎችም ከአቶ ተመስገን ጋር አሶሳ ተገኝተዋል።
በክልሉ በሚኖራቸው ቆይታ የግብርና እና የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎችን ጨምሮ ሌሎች የልማት ሥራዎችን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል፡፡
አቶ ተመስገን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ “የታላቁ ህዳሴ ግድብ መገኛ፣ የንጉስ ሼህ ሆጀሌ ሀገር፣ የወርቋ ምድር ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ገብተናል፤ በቆይታችንም በክልሉ የሚገኙ ልዩ ልዩ የልማት ስራዎችን የምንጎበኝ ይሆናል” ብለዋል፡፡
በአሶሳ የሞቀ አቀባበል ላደረጉላቸው የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር እና ካቢኔያቸው እንዲሁም የአሶሳ ከተማ ሕዝብም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በፍሬሕይወት ሰፊው