የአዲስ አበባ ካቢኔ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ካቢኔ ባካሄደው 3ኛ ዓመት 14ኛ መደበኛ ስብሰባ በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
ካቢኔው ተወያይቶ ውሳኔ ያሳለፈባቸው ጉዳዮች ቀጥለው ቀርበዋል፡-
- የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር በከተማዋ የሚገኙ ዋና ዋና መንገዶች ላይ ባሉ የሴት ባክ (setback) ፕላን ትግበራ ከመንገድ ያላቸው ርቀት መጠን በካቢኔ ወስኖ ወደ ትግበራ መግባቱ ይታወሳል ።
ከዚህ በፊት የተወሰኑ የሴት ባክ ለማስተግበር፤ ሂደቱን ለማሳለጥ እና አገልግሎቱን ለማፍጠን የቀረቡ በደንብ የተደገፉ ማብራሪያዎችን በጥልቀት ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።
- የመንገድ ዳር መብራት እና መሠረተ-ልማቶች ለማሥተዳደር የሚችል አሥተዳደር ኤጀንሲ ማቋቋሚያ ደንብ መርምሮ አጽድቋል፡፡
በዚህም የመንገድ ዳር መብራቶች እና መሠረተ-ልማቶች ስንታንዳርዶችን ማውጣት፣ መቆጣጠር እንደ አስፈላጊነቱም በሚወጣው መመሪያ መሠረት ተገቢውን የቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርግ ይሆናል።
- የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን አደረጃጀት አሠራር ማሻሻያ ደንብ ጸድቋል፡፡
በይዘቱም ከተማዋ ከጊዜው ጋር የሚመጥን የፅዳት አጠባበቅ፣ አጠቃቀም እና የቆሻሻ አወጋገድ እና የተሽከርካሪ የመንገድ አጠቃቀም እንዲሁም የመንገድ ፍሳሽ አወጋገድ አላግባብ የመንገድ ላይ የመፀዳዳት ተግባራትን እንዲጠበቁ የሚያደርጉ የሕግ ማዕቀፎች እና ተጥሰው ሲገኙ ለማስከበር ሕገ-ወጥ አሠራሮችን ለመቅጣት የሚያግዙ የሕግ ማዕቀፎችን የያዘ ነው፡፡