Fana: At a Speed of Life!

የሁቲ አማጺያን በመርከብ ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸማቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በየመን የሚንቀሳቀሱት የሁቲ አማፂያን ዛሬ ረፋድ ላይ በፈጸሙት የሰው አልባ ድሮን ጥቃት በቀይ ባህር ትጓዝ በነበረች መርከብ ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ተነገረ።

ጥቃቱ የሁቲዎችን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረው እና ለሚፈፀሙ ጥቃቶች ምላሽ ሲሰጥ የቆየው የአሜሪካ ባህር ሀይል ከስምንት ወራት በኋላ ከአካባቢው መልቀቁን ተከትሎ የተፈፀመ መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡

በጥቃቱ ወደ እስያ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና አውሮፓ ገበያዎች በሚወስደው ወሳኝ የንግድ መስመር ላይ እቃ የጫነች የላይቤሪያን ሰንደቅ ዓላማ የምታውለበልብ መርከብ ጉዳት ደርሶባት መታየቷ ተነግሯል።

የእንግሊዝ የባህር ንግድ ኦፕሬሽን ማእከል እንዳስታወቀው÷ ጥቃቱ በአማፂያኑ ቁጥጥር ስር በምትገኘው ሆዴይዳ የወደብ ከተማ ዳርቻ ዛሬ ረፋድ ላይ መፈፀሙን አስታውቋል፡፡

በጥቃቱ በአንድ እቃ ጫኝ መርከብ ላይ ጉዳት ሲደርስ በመርከበኞች ቡድን ላይ ግን የደረሰ ጉዳት የለም ብሏል፡፡

መርከቧ ኮንቴነር ጫኝ መርከብ ስትሆን ከመካከለኛው ምስራቅ ወደ ቻይናዋ ችንጋዶ ከተማ ስትጓዝ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

አማፂያኑ በዋናነት በቀይ ባህር በሚንቀሳቀሱ እና የእስራኤል፣ አሜሪካ እና ብሪታኒያ ይዞታ በሆኑ መርከቦች ብቻ ጥቃት እንደሚፈፅሙ ቢገልጹም ከተጠቀሱት ሀገራት ጋር ግንኙነት የሌላቸው መርከቦችም የጥቃቱ ኢላማ መሆናቸው እየተነገረ ነው።

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የምታካሂደውን ዘመቻ ካላቆመች አማፂያኑ ጥቃታቸውን አጠናክረው እንሚቀጥሉ መግለፃቸውን ኤቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.