Fana: At a Speed of Life!

በሐረሪ ክልል በመሰረተ ልማት ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል በመሰረተ ልማት ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።

በርዕሰ መስተዳድሩ ኦርዲን በድሪ የተመራ የክልሉ ካቢኔ አባላት በሐረር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

የካቢኔ አባላቱ በጉብኝታቸው የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች፣ የከተማ ፅዳት እና ውበት፣ የጀጎል ቅርስ መልሶ ልማት ሥራዎች እና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ተመልክተዋል፡፡

አቶ ኦርዲን በድሪ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ÷ከተማዋን ፅዱ፣ ውብ እና ለኢንቨስትመን ምቹ በማድረግ ረገድ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች አበረታች ናቸው።

ከተማዋን በስትራቴጂክ የልማት ዕቅድ ለመምራት የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ቅንጅታዊ አሰራር በማጎልበት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አክለዋል።

በተለይ በቅርቡ በከተማው በሚከበረው የሐረር ቀን በርካታ ፕሮጀክቶችን አስመርቆ አገልግሎት ለማስጀመር ዕቅድ መያዙን ጠቁመው÷ በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በጊዜ የለኝም መንፈስ ቀን ከሌት መረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በከተማው ግንባታ ጀምረው ያቋረጡ ባለሃብቶች ግንባታቸውን በማጠናቀቅና ወደ ሥራ እንዲገቡ አስፈላጊውን የቁጥጥር ስራ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

መሬት ወስደው ባላለሙ ባለሃብቶች ላይ ህግን መሰረት ያደረገ አስተማሪ እርምጃ እንደሚወሰድ መግለጻቸውንም የክልል ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

በሌላ በኩል የከተማዋን ገፅታ እያበላሹ የሚገኙ በግድግዳ ላይ ማስታወቂያዎችን በአግባቡ በማስተዳደር የተጀመሩ ውጤታማ ሥራዎችን ማጠናከርና የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባሻገርም በህገ ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ ላይ የተጀመረው ሥራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

በቅርቡ ለሚጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን ጠብቆ በመንከባከብ የከተማዋን ገፅታ መቀየር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.