ግለሰብን በማገት ዶላርና የተለያዩ ንብረቶችን ወስደዋል የተባሉ 3 የፖሊስ አባላት ላይ ክስ ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ግለሰብን አስገድደው ተሽከርካሪ ውስጥ በማገት ዶላርና የተለያዩ ንብረቶቹን ወስደዋል የተባሉ ሶስት የፖሊስ አባላት ላይ ክስ ተመሰረተ።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ኮንስታብል ክብሩ በለጠ ጫማ፣ ረ/ሳጅን ያለምሰው ዱሬ ጤናው እና ረ/ሳጅን ባህረዲን አለሙ አህመድ በተባሉ የፖሊስ አባላቶች ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና ለ እንዲሁም የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 9 ንዑስ ቁጥር 1 ስር የተደነገጉ ድንጋጌዎችን ተላልፈዋል በማለት ክስ አቅርቦባቸዋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ መምሪያ የፖሊስ አባላቱ ተሳትፈዋል በተባሉበት የወንጀል ድርጊት ተግባር ተከታትሎ በምርመራ በማጣራትና የምስክር ቃል ተቀብሎ የምርመራ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ አስረክቧል።
በዚህም ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ዝርዝር ክስ ላይ እንደተመላከተው፤ 1ኛ ተከሳሽ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ መምሪያ የተጠርጣሪ አስተዳደር ስር የጥበቃ አባል፣ 2ኛ ተከሳሽ የተጠርጣሪ ክትትልና ኦፕሬሽን ክፍል የኢኮኖሚ ነክ ጉዳዮች ወንጀሎች የፍርድ ቤት አስገዳጅ አባል፣ 3ኛ ተከሳሽ በፎረንሲክ ምርመራ መምሪያ ስር በሹፌርነት ሲሰሩ ነበር።
ተከሳሾች ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ፣ ወይም በሌላ ሰው መብት ወይም ጥቅም ላይ ጉዳት እንዲደርስ ለማድረግ በማሰብ በሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰዓት አካባቢ በየካ ክ/ከ ወረዳ 8 ጆን ጋራዥ አካባቢ ካልተያዘ ሲቪል ከለበሰ ግብረአበራቸው ጋር በመሆን አንድ የግል ተበዳይን አስገድደው 3ኛ ተከሳሽ ለስራ አላማ የተረከበው ተሽከርካሪ ውስጥ በማገት፣ ከግል ተበዳዩ 2 ሺህ 600 ዶላር፣ ሁለት የእጅ ስልክ እና 50 ሺህ ብር አስገድደው በመውሰድ ከተሽከርካሪው ገፍትረው ጥለውት መሄዳቸው በክሱ ተመላክቷል።
በዚህም በዋና ወንጀል አድራጊትና በወንጀሉ ድርጊት በሚሰጠው ውጤት ሙሉ ተካፋይ በመሆን፣ የፖሊስ ስልጣናቸውን ተጠቅመው ያለአግባብ የፈጸሙት የወንጀል ድርጊት መሆኑ ተጠቅሶ ክስ ቀርቦባቸዋል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በዐቃቤ ሕግ የተመሰረተውን ክስ ዝርዝር ለተከሳሽ እንዲደርስ ካደረገ በኋላ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ በማዘዝ ለሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ