ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የምክር ቤት አባላትን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ አሳሰቡ።
የምክር ቤቱ አባላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ አፈ-ጉባዔው ባደረጉት ንግግር÷ መድረኩ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አፈፃፀም፣ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ፣ አሥተዳደራዊ ሕግ እና የፌዴራል መንግሥት የመካከለኛ ጊዜ የኢንቨስትመንት ዕቅድ ላይ እንደሚያተኩር አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ በስኬት የተከናወነው የምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ ማሰባሰብ ተግባር በክልሎችም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡
የታለመው ሀገራዊ መግባባት እውን እንዲሆንም በክልሎች ተመሳሳይ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚጠበቅ ገልጸው÷ ለምክክሩ ስኬትም የምክር ቤት አባላትን ጨምሮ እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
እንዲሁም በሀገሪቱ ተደራራቢ እየሆኑ የመጡ ቁርሾዎች እልባት እንዲያገኙ የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ማዕቀፍን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
በፌደራል ደረጃ የተዘጋጀውና በሀገሪቱ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችላል የተባለው የአሥተዳደራዊ ሕግን ክልሎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል::