በአማራ ክልል የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በቅንጅት ለመፍታት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በየደረጃው ያሉ አመራር አባላት የጋራ ግብን መሠረት በማድረግ የሰላምና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በቅንጅት ለመፍታት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
ለሁለት ቀናት የሚቆይ በወቅታዊ የሰላምና መልካም አሥተዳደር ሥራዎች ላይ የሚመክር መድረክ የክልል፣ የዞንና የከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ አመራር አባላት በተገኙበት በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
አቶ አረጋ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ባለፉት ቀናት ከክልል፣ ከዞንና ከከተማ አሥተዳደር አመራር አባላት ጋር በወቅታዊና መሠረታዊ ችግሮች ላይ ምክክር መደረጉን አስታውሰዋል፡፡
ውይይቶቹም በትምህርት የገጠመውን ሥብራት ለመጠገን፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማትን ለማሳካትና ሌሎች የክረምት ሥራዎችን ለማከናወን ያለሙ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ምልአተ-ሕዝቡን ያሳተፈ የሰላም ጥሪ ለማቅረብ የሚያስችል ውይይት በማካሄድ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት “የሰላም አመቻች አደረጃጀት” መፍጠር መቻሉንም አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይም የክረምቱን መግባት ተከትሎ የሚከሰቱ እንደ ወባ፣ ኮሌራና ሌሎች በሽታዎችን በመከላከልና ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ ለልማት ጥቅም ላይ ለማዋል አቅጣጫ እንደሚሰጥ አመላክተዋል፡፡
ይህም በክረምቱ የሚካሄዱ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን በብቃት በመፈጸም የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የዛሬው የምክክር መረድክም ያለፉት መድረኮች ማጠቃለያ፣ የቀጣይ የክረምት ወራት ሥራ ማስጀመሪያና የ2017 በጀት ዓመት ተግባራትን ከወዲሁ ተገንዝቦ ለመሥራት የሚያነሳሳ ነው ብለዋል፡፡
በየደረጃው ያሉ የአመራር አባላት የጋራ ዓላማና ግብ በመሰነቅ የክልሉን የሰላም ሁኔታ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚያሻግር ሥራ በቁርጠኝነት ማከናወን እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡