ስፖርትና ኪነ-ጥበብ የአፍሪካውያንን ግንኙነትን ለማጠናከር የማይተካ ሚና አላቸው – አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ስፖርትና ኪነ-ጥበብ የአፍሪካውያንን የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከር የማይተካ ሚና እንዳላቸው የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገለጹ።
የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊና የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ የሸነን አፍሪካ ፌስቲቫልን መርቀው ከፍተዋል።
በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ በቱሪዝም ሚኒስቴርና በሸነን አፍሪካ ትብብር በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተዘጋጀው ፌስቲቫል ላይ የቀድሞዎቹ የናይጄሪያ ኮከብ ተጫዋቾች ኑዋንኮ ካኑ፣ ዳንኤል አሞካቺና ሴኔጋላዊው ሄንሪ ካማራን ተገኝተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የአህጉሪቷ የኪነ-ጥበብ ከያንያን፣ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተፅዕኖ ፈጣሪዎች፣ ዲዛይነሮች፣ የቅርጽ ተወዳዳሪዎች (ሞዴሎች)፣ የቴክኖሎጂ ሙያተኞች፣ ባለ ሃብቶች፣ ዲፕሎማቶች እና በተለያየ የሙያ ዘርፍ የሚሰሩ ግለሰቦች ታድመዋል።
በፌስቲቫሉ መክፈቻ ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፤ በቱሪዝም፣ ስፖርት እና ፋሽን ላይ ትኩረት ያደረጉ አህጉራዊ ሁነቶች አፍሪካዊ ግንኙነትና ትብብርን ለማጠናከር የማይተካ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
ፌስቲቫሉ በዓድዋ ድል መታሰቢያ የተዘጋጀው ቅድመ አያቶች ቅኝ ግዛትን ለመፋለም መሰረት የጣሉበት መሆኑን ለማስገንዘብ እንደሆነ ተናግረዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ፤ ፌስቲቫሉ ለተሳታፊ አፍሪካውያን የስፖርት ጨዋታን ጨምሮ የመዲናዋን የቱሪዝም መዳረሻ በማስጎብኘት ኢትዮጵያን የበለጠ ለማስተዋወቅ ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።
ፌስቲቫሉም የአፍሪካውያንን የእርስ በእርስ ትስስርና አንድነት በማጠናከር የኢትዮጵያን እምቅ ጸጋ ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቅርስ፣ ባህል፣ ወግ እና እምቅ ጸጋዎች በማስተዋወቅ አፍሪካውያን ኢትዮጵያን መጥተው የሚጎበኙበትን ዕድል ማስገንዘብ ያስችላል ብለዋል።
የሸነን አፍሪካ በኢትዮጵያ መስራችና ስራ አስፈፃሚ ዳግም ጥበቡ፤ የኢትዮጵያና የአፍሪካን ምርት፣ ቱሪዝምና ስፖርት ማነቃቃት ዓላማቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በፌስቲቫሉም በስፖርት፣ በኪነ-ጥበብና ሌሎች ዘርፎች ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው አፍሪካዊያንን በመጋበዝ የፓን አፍሪካኒዝም ትስስርን ለማጠናከር ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።