Fana: At a Speed of Life!

26ኛው ዓለም አቀፍ የሐረር ቀን እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 26ኛውን የሐረር ቀን ምክንያት በማድረግ በሐረር ከተማ የንግድ ትርዒት እና ባዛር ተከፍቷል።

በንግድ ትርዒት እና ባዛሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፣አስመጪ እና አከፋፋዮች እንዲሁም አምራች ኢንተርፕራይዞች ተሳትፈዋል።

መርሐ ግብሩ በሐረሪ ያለውን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የኢኮኖሚ መነቃቃትን ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰመስተዳድር ኦርዲን በድሪ ÷ ኢንዱስትሪዎችና አምራች ኢንተርፕራይዞች ምርት እና ምርታማነታቸውን አሳድገው ለኢኮኖሚው አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

26ኛው ዓለም አቀፍ የሐረር ቀንም የማህበራዊ መስተጋብርን በማጠናከር በኢኮኖሚው ፈጣን እድገት ለማስመዝገብ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አንስተዋል

የተረጋጋ አከባቢን በመፍጠር ለኢኮኖሚ እድገት በቁርጠኝነት እንሰራለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በበዓሉ ላይ ለተሳተፉ ዳያስፖራዎች ቦታ ማቅረብን ጨምሮ የተለያዩ ማበረታቻዎች እንደሚሰጡ ገልፀዋል።

የተጀመሩት የልማት ሥራዎች ለአንድ ሰሞን ብቻ ሳይሆን የዕለት ተዕለት ተግባር ሆነው እንደሚቀጥሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.