ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት ተግባራዊ ምላሽ ይገባል ብላ ታምናለች – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለማስተካከልና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ተግባራዊ ምላሽ ይገባል ብላ ታምናለች ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የኢትዮጵያ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዕቅድ ትግበራን በይፋ ሲያስጀምሩ ነው።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ጉዳይን አንዱ የልማት አጀንዳ በማድረግ እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸው፤ በአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ኢትዮጵያ ከሀገር አልፋ ጎረቤት ሀገራትንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራ በመተግበር ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡
በአየር ንብረት ለውጥን የማይናወጥ ኢኮኖሚን ለመገንባትና አጣጥሞ ለመሄድ በየደረጃው የሚገኝ አመራር በትኩረትና በሀላፊነት መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ዕቅዶችን እውን ለማድረግ የወጡ ህጎችና ፖሊሲዎችን ወደ ተግባር መቀየር፣ ፈንድ ማፈላለግና የስራዎችን ውጤት ገምግሞ የተሻለ አፈጻጸም እውን ማድረግ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ይህ ትግበራ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ለመቅረጽ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
ግብና አላማዎችን በማስቀመጥ ወደ ተግባር መቀየርና አፈጻጸሙን ገምግሞ ውጤት ማምጣት የሁሉንም ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
በመድረኩ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ያላት መልክና በሚፈጠሩ ችግሮች ተጋላጭነቷ ምን ድረስ እንደሆነ፣ ይህን ለመከላከል እየተገበረቻቸው ያሉ ስራዎችን የሚያሳዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል።
በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተው የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመከላከል ሀገራት መውሰድ ያለባቸው ሃላፊነት ተብለው በፓሪሱ ስምምነት ከተቀመጡ ውስጥ አንዱ ነው።
የኢትዮጵያ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዕቅድ ለሁለተኛ ጊዜ ተሻሽሎ የተዘጋጀና ዕቅዱ ከ2013 እስከ 2022 የሚሸፍን ይሆናል።
በዕቅድ ትግበራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ሚኒስትሮች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ተቋማት የዘርፉ ተዋናዮች ተገኝተዋል።
በፍሬህይወት ሰፊው