ዓለም አቀፍ የሐረር ቀንን ምክንያት በማድረግ ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 26ኛው ዓለም አቀፍ የሐረር ቀንን ምክንያት በማድረግ በሐረር ከተማ “ለሀገራችን ሰላምና ብልፅግና የዲያስፖራው ሚና” በሚል ሃሳብ ሲምፖዚየም እየተካሄደ ይገኛል።
በሲምፖዚየሙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ የሀረሪ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ሱልጣን አብዱሰላም ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮች፣ ዳያስፖራዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀረር ነዋሪዎችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ይገኛል።
ሲምፖዚየሙ በዋናነት የሀገርን ገፅታ ለመገንባትና ዳያስፖራው ስለ ሀገሩ የተሻለ ግንዛቤ የሚያሰፋበት እንደሚሆን ከሀረሪ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በሲምፖዚየሙ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ÷ አለም አቀፉ የሀረር ቀን ዳያስፖራው ማህበረሰብ ከሀገሩ ጋር ያለው ትስስር ይበልጥ እንዲጎለብት ብሎም በሀገሩ ልማት ላይ አሻራውን እንዲያኖር እያስቻለ መሆኑን ገልፀዋል።
የክልሉ ዳያስፖራ በሀገሩ ጉዳይ በንቃት ተሳትፎ በማድረግና በክልሉ የልማት ስራ ላይ እያደረገው ያለው ተሳትፎ በአርዓያነት የሚጠቀስ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ዳያስፖራው ባህሉና ትውፊቱ ሳይበረዝ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ እያደረገ ያለውን ጥረት ድንቀው የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል የጠየቁ ሲሆን÷ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ዳያስፖራውን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡