Fana: At a Speed of Life!

ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሰሩ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የዕውቅና መርሐ ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሰሩ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የዕውቅና መርሐ ግብር በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተካሄደ።

በንግድ ሚዲያ ዘርፍ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ኤፍ ቢ ሲ) በዘርፉ ለነበረው አስተዋጽኦ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት “ሚዲያ ለሀገር” በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው ይህ የዕውቅና መርሐ ግብር መገናኛ ብዙሃን ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ይበልጥ እንዲተጉ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተነግሯል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ መገናኛ ብዙሃን በመረጃ ላይ ተመርኩዘው የሀገርን ክብርና ጥቅም ለማስጠበቅ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

አንድነትን፣ ፍቅርን እና የጋራ ትርክትን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

በመርሐ ግብሩ ለሽልማት ከተመረጡት 69 መገናኛ ብዙሃን 11ዱ የዋንጫና የምስክር ወረቀት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅ ተቀብለዋል።

በዚህም በንግድ ሚዲያ ዘርፍ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (ኤፍ ቢ ሲ)፣ አዲስ ዋልታ እና ኢቢኤስ ተሸላሚ ሲሆኑ፤ በመንግስት ሚዲያ ዘርፍ ኢቢሲ፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ ኦቢኤን እና አሚኮ ዋንጫ ተሸልመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ልዩ ተሸላሚ እንዲሁም አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.