በክልሉ 60 ሺህ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል – አቶ ደስታ ሌዳሞ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲዳማ ክልል በ2017 በጀት ዓመት 60 ሺህ የሥራ እድል ለመፍጠር መታቀዱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለፁ፡፡
ርዕሰ መስተዳደሩ በክልሉ 6ኛ ዙር 3ኛ የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የ2017 በጀት አመት እቅድን አቅርበው ውይይት ተካሂዷል።
በበጀት ዓመቱ የክልሉን ኢኮኖሚ በ10 ነጥብ 3 በመቶ ከፍ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸው፤ የክልሉ አጠቃላይ ኢኮኖሚ 43 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆነው በግብርና 21 ነጥብ 1 በመቶው በኢንዱስትሪ እንዲሁም 36 ነጥብ 2 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በአግልገሎት ዘርፍ እንደሚሸፈን ጠቁመዋል፡፡
በተለይም በግብርና ዘርፍ ምርታማነትን በመጨመር፣ የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ፣ ገበያን ማረጋጋት እና ምርት ወደ ማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ በኢትዮጵያ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ላይ ክልሉ የድርሻውን ለማበርከት ይሰራል ብለዋል፡፡
በእንስሳት ልማት ዘርፍ በላሞች ዝርያ ማሻሻል፣ በዶሮ እርባታ፣ በንብ ማነብ፣ በሀር ትል፣ በፍየል እና በግ ዝርያ ማሻሻል እንዲሁም በዓሣ ሀብት ዙሪያ በትኩረት ለመስራት መታቀዱን አመላክተዋል፡፡
የሥራ እድል ፈጠራ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳደሩ÷ 60 ሺህ ያህል የሥራ እድል ለመፍጠር እቅድ መያዙን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ የሆኑ 5 ሺህ የክልሉ ተወላጆች የሙያ ስልጠና እንደሚሰጣቸውም ጠቁመዋል፡፡
የሀዋሳ ከተማን አረንጓዴ በማድረግ እና መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ሥራ ከህብረተሰቡ ጋር ተባብሮ ለመሥራት እቅድ መነደፉን አመላክተዋል፡፡
በጤናው ዘርፍ የእናቶችና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ፣ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት፣ የመድኃኒት አቅርቦትን ማሻሻልና መሰል የጤና ተግባራት እንደሚከናወኑ አስገንዝበዋል፡፡
ምክር ቤቱ ከርዕሰ መስተዳድሩ በቀረበው 2017 በጀት አመት እቅድ ላይ ተወያይቶ ያፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡