የገበታ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን አስደናቂ ውበት ገልጠዋል- አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የገበታ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን አስደናቂ ውበት የገለጡና የህልምን ትልቅነት ያሳዩ መሆናቸውን የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገለጹ።
የጎርጎራ ፕሮጀክት ግንባታ ተጠናቅቆ ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መመረቁ ይታወቃል።
ይህን ተከትሎም አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እንዳሉት የገበታ ፕሮጀክቶች የቱሪዝም ዘርፉን የሚያሳድጉና ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ የሚያደርጉ ናቸው።
በተለይም በመሰረተ ልማት ግንባታ በጥራት መስራት የተቻለበትና የተጓደሉትንም ማሟላት የተቻለበት መሆኑን ጠቅሰው÷ የኢትዮጵያን የተደበቀ ውበት የገለጡና የህልምን ትልቅነት ያሳዩ ናቸው ብለዋል፡፡
የፕሮጀክቶቹ ክንውን የላቀ ተስፋና ነገን ተሻግሮ ማሰብና ማደግ የሚቻል መሆኑን በተግባር ያሳየ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የገበታ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻዎች ያሰፉ በተፈጥሮ ውበት ላይ ጥበብ በመጨመር የበለጠ ማስዋብና ማራኪ ስፍራ ማድረግ የሚቻል መሆኑን አሳይተዋል ነው ያሉት፡፡
በሁሉም ዘርፍ የልማት ህልሞች ትልቅነትና ተወዳዳሪነት እያደገ የመጣበት ሁኔታ ስለመፈጠሩ አንስተው÷ የጎርጎራ ፕሮጀክት ለዚህ ጥሩ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ለኢትዮጵያ የቱሪዝም እድገት ተጨማሪ አቅም መሆኑን አስረድተው÷ ከውጭም ይሁን ከሀገር ውስጥ ቱሪስቶች የጎርጎራን አስደናቂ ውበት እንዲጎበኙት ጋብዘዋል።