መቻል የሰራዊቱ የስነ-ልቦና ጥንካሬ መሠረት ሆኖ እንዲቀጥል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ -ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መቻል የስፖርት ክለብ የቀድሞ ታሪኩን አድሶ እና በውጤት ታጅቦ የሰራዊቱ የስነ-ልቦና ጥንካሬ መሠረት ሆኖ እንዲቀጥል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ በመቻል 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
የመቻል ስፖርት ክለብ ሀገራችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ በኩራት ያስጠሩ ዕንቁ ስፖርተኞችን ያፈራ የሕዝብ ክለብ ነው ያሉት አቶ ተመስገን ለአብነትም÷ አበበ ቢቂላን፣ ማሞ ወልዴን፣ ምሩፅ ይፍጠርን፣ ጌጤ ዋሜን እና አልማዝ አያናን ለሀገር ያበረከተ ባለውለታ ክለብ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ይህ ድንቅ ክለብ የክብር ዘባችን የሆነው የመከላከያ ሰራዊታችን የድል አድራጊነት ምልክታችን እና ተምሳሌታችን ጭምር ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
በመሆኑም ይህ ገናና የስፖርት ክለብ የቀድሞ ታሪኩን አድሶ እና በውጤት ታጅቦ የሰራዊቱ የስነ-ልቦና ጥንካሬ መሠረት ሆኖ እንዲቀጥል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት፡፡